2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32

32
የሰናክሬም ወረራ
1ከዚህም ነገርና በታማኝነት ከተደረገው ነገር በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፥ በተመሸጉትም ከተሞች ፊት ሰፈረ፥ የራሱም ሊያደርጋቸው አሰበ። 2ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደመጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ሊወጋ ፊቱን አንዳቀና ባየ ጊዜ፥ 3ከከተማይቱ በስተ ውጭ ያለውን የውኃውን ምንጭ ለመድፈን ከሹማምንቱና ከኃያላኑ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት። 4እጅግም ሰዎች ተሰብስበው፦ “የአሦር ነገሥታት መጥተው ብዙ ውኃ ለምን ያገኛሉ?” ብለው ምንጩን ሁሉ፥ በምድርም መካከል ይንዶለዶል የነበረውን ዥረት ደፈኑ። 5ንጉሥ ሕዝቅያስም ራሱን ለሥራ ጽኑ አደረገ፥ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፥ በላዩም ግንብ ሠራበት፥ ከእርሱም በስተ ውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ በዳዊትም ከተማ ያለችውን ሚሎን አጠነከረ፤ ብዙም የጦር መሣሪያና ጋሻ ሠራ። 6የጦር አዛዦቹንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ፥ ሁሉንም በከተማይቱ በር ወዳለው አደባባይ ሰበሰበ፥ እንዲህም ብሎ አበረታታቸው፦ 7“ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና የአሦርን ንጉሥና ከእርሱ ጋር ያለውን ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። 8ከእርሱ ጋር ያለው ሥጋዊው ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን ጌታ አምላካችን ነው።” ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃላት ተበረታታ።
9ከዚህም በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በለኪሶ ሳለ ባርያዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ወደ ይሁዳ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ፦ 10“የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፦ ‘እናንተ በማን ተማምናችሁ በኢየሩሳሌም ምሽግ ትቀመጣላችሁ? 11“ጌታ አምላካችን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል” እያለ በራብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ለመስጠት የሚያባብላችሁ ሕዝቅያስ አይደለምን? 12“በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፥ በእርሱም ላይ ዕጠኑ” እያለ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አዝዞ፥ የኮረብታው መስገጃዎቹና መሠዊያዎቹን ያፈረሰ ይህ ሕዝቅያስ አይደለምን? 13እኔና አባቶቼ በምድር አሕዛብ ሁሉ ያደረግነውን አላወቃችሁምን? የምድርስ ሁሉ አሕዛብ አማልክት አገራቸውን ከእጄ ለማዳን በውኑ ችለዋልን? 14አባቶቼ ካጠፉአቸው ከአሕዛብ አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄ ለማዳን የቻለ ማንስ ነበር፤ እናንተንስ አምላካችሁ ከእጄ ለማዳን የሚችል ይመስላችኋልን? 15አሁንም ሕዝቅያስ አያስታችሁ፥ እንዲህም አያባብላችሁ፥ አትመኑትም፤ ከአሕዛብና ከመንግሥታት አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄና ከአባቶቼ እጅ ለማዳን ማንም አልቻለም፤ ይልቁንስ አምላካችሁ ከእጄ ሊያድናቸሁ እንዴት ይችላል?’ ”
16ባርያዎቹም ደግሞ አምላክ በሆነው በጌታና በባርያው በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ። 17ደግሞም የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመስደብ፥ በእርሱም ላይ ለመናገር፦ “የምድር አሕዛብ አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ ለማዳን እንዳልቻሉ፥ እንዲሁ የሕዝቅያስ አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድን አይችልም” የሚል ደብዳቤ ጻፈ። 18ከተማይቱንም ወርሮ ለመውሰድ፥ በቅጥርም ላይ የተቀመጡትን የኢየሩሳሌም ሕዝብ ለማስፈራራትና ለማስደንገጥ፥ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ይጮኹባቸው ነበር። 19በሰውም እጅ በተሠሩ በምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደሚናገሩ መጠን በኢየሩሳሌም አምላክ ላይ ተናገሩ።
ሰናክሬም መሸነፉና መሞቱ
20ንጉሡም ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ነገር ጸለዩ፥ ወደ ሰማይም ጮኹ። 21ጌታም ጽኑዓን ኃያላኑንና መሳፍንቱን የጦር አዛዦቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር እንዲያጠፋ መልአኩን ላከ። የአሦርም ንጉሥ አፍሮ ወደ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩም ቤት በገባ ጊዜ ከአብራኩ የወጡት ልጆቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት። 22እንዲሁም ጌታ ሕዝቅያስንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካለው ሁሉ አሳረፋቸው። 23ብዙዎቹም ለጌታ መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፥ ለይሁዳም ንጉሥ ለሕዝቅያስ እጅ መንሻ ይሰጡ ነበር፤ እርሱም ከዚህ ነገር በኋላ በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።
ንጉሥ ሕዝቅያስ መታመሙ
24በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስኪሞት ድረስ ታመመ፥ ወደ ጌታም ጸለየ፤ እርሱም ተናገረው፥ ምልክትም ሰጠው። 25ሕዝቅያስ ግን እንደ ተቀበለው ቸርነት መጠን አላደረገም፥ ልቡም ኰራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ በኢየሩሳሌምም ላይ ቁጣ ሆነ። 26ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኩራት ራሱን አዋረደ፥ የጌታም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።
የንጉሥ ሕዝቅያስ ሀብትና ስኬት
27ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀበትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቁና ለሽቶው፥ ለጋሻውና ለከበረው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶች ሠራ። 28ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንሰሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ። 29ጌታም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ሠራ፥ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ። 30ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፥ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። የሕዝቅያስም ሥራ ሁሉ ተከናወነ። 31ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በአገሩ ላይ ስለተደረገው ተአምራት ለመጠየቅ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ ጌታ እርሱን ለመፈተንና በልቡ ያለውን ሁሉ ለማወቅ ሲል ተወው።
32የሕዝቅያስም የቀረው ነገር፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 33ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ ታላቅ የቀብር ሥርዓት አደረጉለት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ