2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 31

31
የአሕዛብ መቅደሶች መፍረሳቸው
1ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በዚያ የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው ሁሉንም ፈጽመው እስከሚያጠፏቸው ድረስ ሐውልቶቹን ሰባበሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጡ፥ በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኮረብታው መስገጃዎችና መሠዊያዎች አፈረሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ።
2ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው አቆመ፤ በጌታ ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ እንዲያገለግሉ፥ እንዲያመሰግኑም ክብርም እንዲሰጡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን አቆመ። 3#ዘኍ. 28፥1—29፥39።በጌታም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፈለውን ወሰነ። 4#ዘኍ. 18፥12፤13፤21።የጌታንም ሕግ በጽኑ እንዲያገለግሉ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የሚገባቸውን ድርሻ እንዲሰጡአቸው በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ። 5ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን ጠጅ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ ሁሉ በብዛት ሰጡ፤ የሁሉንም አሥራት በብዛት አቀረቡ። 6በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳም ልጆች የበሬውንና የበጉን አሥራት፥ ለአምላካቸውም ለጌታ የተቀደሰውን አሥራት አመጡ፥ ከምረውም አስቀመጡት። 7በሦስተኛው ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ። 8ሕዝቅያስና ሹማምንቱም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ ጌታንና ሕዝቡን እስራኤልን ባረኩ። 9ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ። 10ከሳዶቅም ወገን የሆነ ታላቁ ካህን ዓዛርያስ፦ “ሕዝቡ ቁርባኑን ወደ ጌታ ቤት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፥ ጠግበናልም፥ ጌታ ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ የተረፈውም ይህ ክምር ትልቅ ነው” ብሎ ተናገረ።
ካህናቱና ሌዋውያኑ ዳግመኛ መዋቀራቸው
11ሕዝቅያስም በጌታ ቤት ውስጥ ግምጃ ቤት እንዲያዘጋጁ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ። 12ቁርባኑና አሥራቱን የተቀደሱትንም ነገሮች በታማኝነት ወደዚያ አስገቡ። ሌዋዊውም ኮናንያ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕረግ ሁለተኛ ነበረ፤ 13በንጉሡም በሕዝቅያስና በጌታ ቤት አለቃ በዓዛርያስ ትእዛዝ ይሒዒል፥ ዓዛዝያ፥ ናሖት፥ አሣሄል፥ ይሬሞት፥ ዮዛባት፥ ኤሊኤል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስ፥ ከኮናንያና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ። 14የሌዋዊውም የይምና ልጅ የምሥራቁ ደጅ ጠባቂ ቆሬ የጌታን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያከፋፍል ሕዝቡ ለጌታ በፈቃድ ባቀረቡት መባ ላይ ተሾመ። 15በካህናቱም ከተሞች ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ድርሻቸውን በታማኝነት እንዲሰጡ ዔድን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማያ፥ አማርያ፥ ሴኬንያ የቆሬ ረዳቶች ነበሩ። 16በትውልዳቸው ከተቈጠሩት በቀር ዕድሜያቸው ሦስት ዓመት የሆናቸውና ከዚያ በላይ የሆኑ በየሰሞናቸውም ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ ጌታ ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፤ 17በየአባቶቻቸውም ቤት ካህናቱ ተቈጠሩ፤ በየሥርዓታቸውና በየሰሞናቸው ዕድሜያቸው ሀያ ዓመት የሆናቸውና ከዚያ በላይ የሆኑ ሌዋውያኑ ተቈጠሩ። 18በታማኝነትም ቅድስናቸውን ጠብቀዋልና ካህነናቱ በየትውልዳቸው ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከወንዶችና ከሴቶች ልጆቻቸው እንዲሁም ከማኅበሩ ሁሉ ጋር ተቈጠሩ። 19በየከተማይቱም ሁሉ በከተማቸው መሰማሪያዎች ውስጥ ላሉ ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ ከካህናቱም ወገን ላሉ ወንዶች ሁሉ፥ በትውልዳቸውም ለተቈጠሩ ሌዋውያን ሁሉ ድርሻቸውን እንዲሰጡአቸው በስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ።
20ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በጌታ ፊት መልካምንና ቅንን ነገር እውነትንም አደረገ። 21ስለ ጌታም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም፥ አምላኩን ለመፈለግ በፍጹም ልቡ አደረገው፥ ተከናወነለትም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ