2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 1

1
ሰሎሞን ጥበብን መጠየቁ
1የዳዊት ልጅ ሰሎሞንም በመንግሥቱ ላይ ራሱን አጸና፤ ጌታ አምላኩም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ እጅግም አገነነው። 2ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች፥ ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ተናገረ። 3ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር ጉባኤው ሁሉ የጌታ ባርያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው መገናኛ ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው ወደ ኮረብታማው ስፍራ ሄዱ። 4#2ሳሙ. 6፥1-17፤ 1ዜ.መ. 13፥5-14፤ 15፥25—16፥1።ለጌታ ታቦት ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎለት ነበርና ዳዊት ከቂርያት-ይዓሪም ወዳዘጋጀለት ስፍራ ታቦቱን አምጥቶት ነበር። 5#ዘፀ. 38፥1-7።የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በጌታ ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር። 6ሰሎሞንም በጌታ ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፥ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
7በዚያም ሌሊት ጌታ፦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ነገር ጠይቀኝ” ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ። 8ሰሎሞንም ጌታን እንዲህ አለው፦ “ለአባቴ ለዳዊት ታላቅና ጽኑ ፍቅር አሳይተኸዋል፥ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል። 9#ዘፍ. 13፥16፤ 28፥14።አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ! ቁጥሩ እንደ ምድር ትቢያ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃልህ ይጽና። 10አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት ለመውጣትና ለመግባት እንድችል ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ሊፈርድ የሚችል ማን ነው?” 11ጌታም መልሶ ሰሎሞንን እንዲህ አለው፦ “ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጸግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልጠየቅህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ እንድትችል ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ጠይቀሃልና፥ 12ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤ ከአንተ በፊትም ከነበሩት ከአንተም በኋላ ከሚነሡት ነገሥታት አንድም እንኳ የሚመስልህ እንዳይኖር አድርጌ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ።” 13ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ከኮረብታው ስፍራ ከመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።
የንጉሥ ሰሎሞን ሠራዊትና የንግድ እንቅስቃሴ
14 # 1ነገ. 4፥26። ሰሎሞንም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፥ አንድ ሺህም አራት መቶ ሰረገሎች፥ ዐሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 15ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። 16#ዘዳ. 17፥16።ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር። 17አንዱም ሠረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ ኀምሳ ሰቅል ብር ከግብጽ ያስመጡ ነበር፤ እነርሱም መልሰው ለኬጢያውያንና ለሶሪያ ነገሥታት ሁሉ ይልኩ ነበር።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ