አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር። ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ በሚግሮን ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤ ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የጌታ ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ሕዝቡም ዮናታን አለመኖሩን አላወቁም ነበር። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ ሁለት ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱ ስም ቦጼጽ ሲሆን፥ ሌላው ሴኔ ተብሎ ይጠራል። ከድንጋዮቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተ ደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር። ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፤ ወደነዚያ ያልተገረዙ ሰዎች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም ጌታ ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን ጌታን የሚያግደው የለምና” አለው። ወጣቱ ጋሻ ጃግሬም፥ “በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል፤ እኔም በሙሉ ልብ ካንተው ጋር ነኝ” አለው። ዮናታንም እንዲህ አለው፥ “እንግዲያውስ ና፤ ወደ ሰዎቹ እንሻገርና እንታያቸው። እነርሱም፥ ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ጠብቁን’ ካሉን፥ ስፍራችንን ይዘን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን፥ ‘ወደ እኛ ኑ’ ካሉን፥ ጌታ እነርሱን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ስለሆነ፥ ወደ እነርሱ እንወጣለን።” ሁለቱም ለፍልስጥኤማውያን ሠራዊት በታዩ ጊዜ፥ ፍልስጥኤማውያን፥ “እነሆ፤ ዕብራውያን ከተደበቁባቸው ጉድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ። የፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ሰዎችም፥ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ የምናሳያችሁ ነገር ይኖራል” ሲሉ በዮናታንና በጋሻ ጃግሬው ላይ ጮኹባቸው። ስለዚህ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፥ “ተከትለኸኝ ውጣ፤ ጌታ በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና” አለው። ዮናታን በእጁና በእግሩ ወደ አፋፉ፥ ጋሻ ጃግሬውን በማስከተል ወጣ። በዮናታንም እጅ ወደቁ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከበስተኋላው እየተከተለ ገደላቸው። ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጀመሪያው ቀን ባደረጉት ግዳያቸው በአንድ ጥማድ የእርሻ ቦታ ላይ ሃያ ያህል ሰዎች ገደሉ። በሰፈር በእርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር። በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ጠባቂዎች፥ የፍልስጥኤም ሠራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች፥ “ሠራዊቱን ቁጠሩና ማን ከዚህ እንደ ሄደ ለዩ” አላቸው። በቆጠሩም ጊዜ፥ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም። ሳኦልም አኪያን፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር። ሳኦል ለካህኑ በመናገር ላይ ሳለ፥ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሁካታው እየጨመረ ሄደ። ስለዚህ ሳኦል ካህኑን፥ “እጅህን መልስ” አለው። ከዚያም ሳኦልና ሰዎቹ ተሰብስበው ወደ ውጊያው ሄዱ። እዚያም ፍልስጥኤማውያን ግራ በመጋባት በታላቅ ትርምስ እርስ በርሳቸው በሰይፍ ይጋደሉ ነበር። እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና አብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደነበሩት እስራኤላውያን ገቡ። በተራራማው የኤፍሬም አገር ተሸሽገው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ፍልስጥኤማውያኑ በሽሽት ላይ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱም አጥብቀው በመከታተል ሊወጉአቸው አሳደዷቸው። በዚያ ቀን ጌታ እስራኤልን ታደገው፤ ጦርነቱም ከቤትአዌን ዘልቆ ሄደ።
1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች