ሳኦል በእስራኤልም ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ እንዲህ ሆነ፤ ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱ ሺህ በማክማስና በተራራማው አገር በቤቴል ከሳኦል ጋር፥ አንዱ ሺህ ደግሞ በብንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ። የቀሩትን ሰዎች ግን ወደ ድንኳኖቻቸው እንዲሄዱ አሰናበተ። ዮናታን ጊብዓ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም፥ “ዕብራውያን ይስሙት!” በማለት በሀገሩ ሁሉ መለከት አስነፋ። እስራኤላውያን ሁሉ፥ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ የተጠሉ ሆኑ” የሚለውን ወሬ ሰሙ። ሕዝቡም ከሳኦል ጋር ለመሰለፍ ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ። ፍልስጥኤማውያን ሠላሳ ሺህ ሠረገሎች፥ ስድስት ሺህ ፈረሰኞች ቁጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሠራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በስተ ምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ። እስራኤላውያን ያሉበት ሁኔታ እጅግ አስጊ መሆኑንና ሠራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፥ በየዋሻውና በየቁጥቋጦው፥ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጉድጓዱ ሁሉ ተሸሸጉ። ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበር፤ አብሮት የተሰለፈው ሠራዊት ሁሉ በፍርሃት ይንቀጠቀጥ ነበር። እርሱም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰዎች መበታተን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሳኦል፥ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። ልክ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ፥ ወዲያውኑ ሳሙኤል ደረሰ፤ እርሱም ሊቀበለው ወጣ። ሳሙኤል ግን “ያደረግኸው ነገር ምንድነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ሠራዊቱ መበታተኑን፥ አንተም በቀጠርኸው ጊዜ አለመምጣትህን፥ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን አየሁ፤ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ወርደው ወደ ጌልገላ ይመጡብኛል፤ እኔም የጌታን ርዳታ አልለመንሁም፥ ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ። ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ ጌታ የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም ባጸናልህ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ ጌታ እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቶአል፤ አንተ የጌታን ትእዛዝ ባለመጠበቅህም፥ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።” ከዚያ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ሄደ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቆጠራቸው፤ ስድስት መቶ ያህል ነበሩ።
1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 13:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች