የሐናኒ ልጅ በሆነው በነቢዩ ኢዩ አማካይነት ጌታ ስለ ባዕሻ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ “እኔ ግን ከትቢያ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ ታዲያ አንተ እንደ ኢዮርብዓም ኃጢአት ሠራህ፤ ሕዝቤንም ወደ ኃጢአት መራህ፤ የኃጢአታቸውም ብዛት የእኔን ቁጣ አነሣሥቶአል። ስለዚህም ኢዮርብዓምን እንዳስወገድኩ አንተንና ቤተሰብህንም አስወግዳለሁ። በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ማንኛውንም የቤተሰብህን አባል ውሾች ይበሉታል፤ በየገጠሩም ሜዳ ላይ የሚሞተውን አሞራዎች ይበሉታል።” ባዕሻ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራዎቹም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ባዕሻ ሞተ፤ በቲርጻም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኤላ ነገሠ። ጌታ በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባዕሻና በቤተሰቡ ላይ ያን የትንቢት ቃል የተናገረበት ምክንያት፥ ባዕሻ በፈጸመው ኃጢአት ጌታን ስላሳዘነ ነበር፤ ባዕሻ ጌታን ያስቆጣውም ከእርሱ ፊት የነበረው ንጉሥ ባደረገው ዓይነት ስለ ሠራው ክፉ ነገር ብቻ ሳይሆን የኢዮርብዓምንም ቤተሰብ ሁሉ በመግደሉ ጭምር ነው። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባዕሻ ልጅ ኤላ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ። የሠረገላዎቹ እኩሌታ ኀላፊ የሆነ ዚምሪ ተብሎ የሚጠራ ከጦር መኰንኖቹ አንዱ በንጉሡ ላይ ዐደመ፤ አንድ ቀን ኤላ በቲርጻ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው አርጻ ተብሎ በሚጠራው ባለሟሉ ቤት ብዙ መጠጥ ጠጥቶ ሰክሮ ነበር። በዚህ ጊዜ ዚምሪ ወደዚያ ቤት ሰተት ብሎ ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነበር። ዚምሪ እንደ ነገሠ ወዲያውኑ የባዕሻ ቤተሰብ አባላት የሆኑትን በሙሉ ገደለ፤ የባዕሻ ዘመድና ወዳጅ የሆነውን ወንድ ሁሉ በሞት ቀጣ። በዚህም ዓይነት ጌታ በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባዕሻ ላይ ባናገረው ትንቢት መሠረት ዚምሪ የባዕሻን ቤተሰብ በሙሉ ፈጀ። ይህም የሆነበት ምክንያት ባዕሻና ልጁ ኤላ ጣዖት በማምለካቸውና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራታቸው የእስራኤልን አምላክ የጌታን ቁጣ በማነሣሣታቸው ነው። ኤላ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዚምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ አድርጎ በእስራኤል ላይ ሰባት ቀን ብቻ ነገሠ፤ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጥኤም የምትገኘውን የጊበቶንን ከተማ ከበው ነበር። ዚምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን በሰሙ ጊዜ በዚያው እንዳሉ ወዲያውኑ የጦር አዛዣቸው የነበረውን ዖምሪን አነገሡ። ዖምሪና ወታደሮቹ የጊበቶንን ከበባ አቆሙ፤ ከዚያም ገሥግሠው ሄደው ቲርጻን ከበቡ። ዚምሪ ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ ክፍል ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበት፤ እርሱም በእሳት ነበልባል ተቃጥሎ ሞተ። ይህ የሆነበት ምክንያት በሠራው ኃጢአት ጌታን በማሳዘኑ ነው፤ እርሱ ራሱ በሠራው ኃጢአትና እስራኤልንም ወደ ኃጢአት በመምራቱ ምክንያት ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ ኢዮርብዓም ጌታን አስቆጥቶአል። ዚምሪ የሠራው ሌላው ነገር ሁሉና ያደረገውም ሤራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚያን ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ወገን በመለየት ከሁለት ተከፍለው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አንደኛው ክፍል ቲብኒ ተብሎ የሚጠራውን የጊናትን ልጅ ለማንገሥ ሲፈልግ፥ ሌላው ክፍል ደግሞ ዖምሪን ለመደገፍ ይሻ ነበር። በመጨረሻም የዖምሪ ደጋፊዎች አሸነፉ፤ ስለዚህም ቲብኒ ተገደለ፤ ዖምሪም ንጉሥ ሆነ። በዚህ ዓይነት አሳ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ አንደኛው ዓመት ዖምሪ በእስራኤል ላይ ነግሦ ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፤ የመጀመሪያዎቹን ስድስት ዓመቶች የገዛውም መኖሪያውን በቲርጻ አድርጎ ነበር። ከዚያም በኋላ ሼሜር ተብሎ ከሚጠራው ሰው የሰማርያን ኰረብታ በስድስት ሺህ ጥሬ ብር ገዛ፤ ዖምሪ ኰረብታውን ከመሸገ በኋላ ከተማ ቆረቆረ፤ ከተማይቱንም ቀድሞ የኮረብታው ባለንብረት በሆነው በሼሜር ስም “ሰማርያ” ብሎ ሰየማት። ዖምሪ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሥታት ይበልጥ የከፋ ኃጢአት በመሥራቱ ጌታን አሳዘነ። እርሱ ራሱ በሠራው ኃጢአትና፥ እንዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአትና ወደ ዋጋ ቢስ ጣዖት አምልኮ በመምራቱ ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ ኢዮርብዓም የእስራኤልን አምላክ የጌታን ቁጣ አነሣሣ። ዖምሪ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉና ያከናወነውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ዖምሪ ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አክዓብ ነገሠ።
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 16:1-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች