1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 15:1-24

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 15:1-24 መቅካእኤ

ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አቢያ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አቢያም፥ እንደ ታላቁ አያቱ እንደ ዳዊት በጌታ ዘንድ ፍጹም ታማኝ ሆኖ በመገኘት ፈንታ፥ አባቱ ሮብዓም ይፈጽመው የነበረውን ኃጢአት ሁሉ መሥራቱን ቀጠለ። ይሁን እንጂ ከእርሱ በኋላ በኢየሩሳሌም እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምንም በሰላም እንዲጠብቅ ጌታ አምላኩ ስለ ዳዊት ሲል ለአቢያ አንድ ወንድ ልጅ ሰጠው። ጌታ ይህን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በሒታዊው ኦርዮን ላይ ከፈጸመው ኃጢአት በቀር ጌታን ደስ የሚያሰኝ ነገር በማድረጉና ትእዛዙንም በብርቱ ጥንቃቄ በመጠበቁ ነው። በአቢያ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፥ በሮብዓምና ኢዮርብዓም ዘመን ተጀምሮ የነበረው ጦርነት ሳያቋርጥ ቀጠለ። አቢያ ያደረገውም ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ አቢያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ አሳ ተተክቶ ነገሠ። ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በሃያኛው ዓመት አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ አንድ ዓመት ገዛ፤ አያቱም ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አሳ፥ የቀድሞ አያቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ ጌታን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። ንጉሥ አሳ በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች የቤተ ጣዖትን አመንዝራዎችን ሁሉ ከሀገሪቱ አስወገደ፤ ከእርሱም በፊት የነበሩ ነገሥታት የሠሩአቸውን ጣዖቶችንም ሁሉ ነቃቅሎ ጣለ። አያቱ ማዕካ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ አጸያፊ ጣዖት ስለ ሠራች ከእቴጌነት ሻራት፤ የሠራችውንም ጣዖት ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በእሳት አቃጠለው። አሳ በኰረብቶች ላይ የሚገኙ የአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎችን በሙሉ ባያስወግድም እንኳ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ለጌታ ታማኝ ሆኖ ኖረ። አባቱ ለጌታ የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸውንና እርሱም ራሱ ከወርቅና ከብር አሠርቶ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ያደረጋቸውን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ በቤተ መቅደስ አኖረ። የይሁዳ ንጉሥ አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ሁሉ በማያቋርጥ የእርስበርስ ጦርነት ላይ ነበሩ። ባዕሻ ይሁዳን በመውረር ራማን ምሽግ አድርጎ መሥራት ጀመረ፤ ይህንንም ያደረገው ወደ ይሁዳ ማንም እንዳይገባና ከዚያም ማንም እንዳይወጣ ለመከልከል ነው። በዚህም ምክንያት ንጉሥ አሳ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ የተረፈውን ወርቅና ብር ሁሉ በማውጣት በባለሟሎቹ እጅ፥ በደማስቆ ከተማ ለነበረው የጣብሪሞን ልጅ፥ የሔዝዮን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፤ ከስጦታውም ጋር እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ፤ “የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዓይነት በመካከላችን የስምምነት ውል እናድርግ፤ ይህም ብርና ወርቅ ለአንተ የላክኹልህ ገጸ በረከት ነው፤ እንግዲህ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ወታደሮቹን ከግዛቴ ያስወጣ ዘንድ እንድትረዳኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አሁን እንድታፈርሰው እለምንሃለሁ።” ንጉሥ ቤንሀዳድም አሳ ባቀረበው ሐሳብ ተስማምቶ የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን በመላክ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፤ እነርሱም ዒዮን፥ ዳን፥ አቤልቤትማዕካና የገሊላ ባሕር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች በገሊላ ባሕር አጠገብ የሚገኘውን አገርና የንፍታሌምን ግዛት ሁሉ ያዙ። ንጉሥ ባዕሻ የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ራማን የመመሸጉ ሥራ እንዲቆም አድርጎ ወደ ቲርጻ ሄደ። ከዚህም በኋላ ንጉሥ አሳ፥ ባዕሻ ራማን ለመመሸግ አከማችቶት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ከዚያ ለማንሣት እንዲረዳው ሕዝቡ አንድም ሳይቀር እንዲመጣ ወደ ይሁዳ ግዛቶች ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ንጉሥ አሳ ከዚያ የተገኘውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ወስዶ ምጽጳንና በብንያም ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የጌባዕን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራበት። ንጉሥ አሳ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ የጀግንነት ሥራውና የመሸጋቸውም ከተሞች ጭምር በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ንጉሥ አሳ በዕድሜ በሸመገለ ጊዜ ግን ከእግሩ ሕመም የተነሣ ሽባ ሆኖ ነበር። እርሱም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮሣፍጥ ነገሠ።