ወደ ሮም ሰዎች 8:19-39

ወደ ሮም ሰዎች 8:19-39 አማ05

ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃል። ፍጥረት ሁሉ ከንቱ እንዲሆን ተፈርዶበታል፤ ይኸውም በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በተስፋ እንዲጠባበቅ ባደረገው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ከጥፋት ባርነት ነጻ ወጥቶ ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር የነፃነትና የክብር ተካፋይ እንደሚሆን ነው። ፍጥረት ሁሉ በአንድ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በምጥ ጭንቀት ተይዞ በመቃተት ላይ መኖሩን እናውቃለን። ነገር ግን በመቃተት ላይ ያለው ፍጥረት ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የተቀበልን እኛም የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን የእግዚአብሔር ልጆች መሆንን በተስፋ እየተጠባበቅን በውስጣዊ ሰውነታችን በመቃተት ላይ እንገኛለን፤ እኛ የዳንነው በዚሁ ተስፋ ነው። ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ የሚታየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ነገር ተስፋ ካደረግን ግን በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም እንዴት መጸለይ እንደሚገባን ስለማናውቅ መንፈስ ቅዱስ በድካማችን ይረዳናል፤ በቃል ሊገለጥ በማይቻል መቃተት ያማልደናል። የሰውን ልብ የሚመረምር አምላክ የመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፤ መንፈስ ቅዱስ ስለ ምእመናን የሚያማልደው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እግዚአብሔርን ለሚወዱና እንደ ፈቃዱም ለተጠሩት ሰዎች እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ለበጎ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። ይህም የሆነበት ምክንያት አስቀድሞ ያወቃቸው ልጁን እንዲመስሉና ልጁም ከብዙ ወንድሞች መካከል በኵር እንዲሆን እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ወሰነ ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውንም አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም አከበራቸው። እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል? እግዚአብሔር ለአንድ ልጁ ሳይራራ ስለ እኛ አሳልፎ ከሰጠው እንዴት ከልጁ ጋር ሁሉን ነገር በነጻ አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቃቸው እርሱ ነው። ማነው የሚፈርድ? ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈርድባቸዋልን? እርሱ ስለ እኛ የሞተ፥ ከሞት ተነሥቶ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠ፥ ስለ እኛም የሚማልድ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል ማነው? ችግር ወይስ መከራ? ስደት፥ ወይስ ራብ? ወይስ ራቊትነት፥ ወይስ አደጋ? ወይስ ሰይፍ? ይህም፥ “ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ በወደደን በክርስቶስ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ድል በመንሣት ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ስለዚህ ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ባለሥልጣኖችም ቢሆኑ፥ አሁን ያለውም ቢሆን፥ በኋላ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኀይሎችም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካገኘነው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}

ከ ወደ ሮም ሰዎች 8:19-39ጋር የተዛመዱ ነፃ የንባብ እቅዶች እና ምንባቦች