ሮሜ 8:19-39
ሮሜ 8:19-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የዓለም ተስፋው የእግዚአብሔርን ልጅ መምጣት ይጠባበቅ ነበርና። ዓለም ባለማወቅ ለከንቱ ነገር ተገዝቶአልና በተስፋ ስለ አስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም። ነገር ግን አስቶ በባርነት ከሚገዛው ከዚህ ወጥቶ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ አገኙአት የነጻነት ክብር ይገባ ዘንድ ተስፋ አለው። እስካሁን ዓለም ሁሉ ያዘነና የተከዘ እንደ ሆነ እናውቃለን። ነገር ግን የሚተክዝ ዓለም ብቻ አይደለም፤ የመንፈስ ቅዱስን ፈለማ የተቀበልነው እናም ደግሞ እናዝናለን እንጂ፤ የነፍሳችንን ድኅነት እናገኝ ዘንድ የልጅነትን ክብር ተስፋ እናደርጋለንና፤ በእምነትም ድነናልና። የሚታየውን ተስፋ ማድረግ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? እንዴትስ ይጠብቃል? የማይታየውን ተስፋ ብናደርግ ግን እርሱን ተስፋ አድርገን በእርሱ እንደ ጸናን መጠን ትዕግሥታችን ይታወቃል። መንፈስ ቅዱስም ከድካማችን ይረዳናል፤ እንግዲያስ ተስፋችንን ካላወቅን ጸሎታችን ምንድነው? ነገር ግን እርሱ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል። እርሱም ልባችንን ይመረምራል፤ ልብ የሚያስበውንም እርሱ ያውቃል፤ ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ ይፈርዳል። እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን። ልጁ በብዙዎች ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቶአቸዋል። ያዘጋጃቸውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ። እንግዲህ ስለዚህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእና ጋር ከሆነ ማን ይችለናል? ለልጁ ስንኳ አልራራም፤ ስለ ሁላችን ቤዛ አድርጎ አሳልፎ ሰጠው እንጂ፥ እንግዲህ እርሱ ሁሉን እንዴት አይሰጠንም? እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማነው? የሚፈርድስ ማነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፥ በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው፥ ደግሞ ስለ እና የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን? መጽሐፍ እንዳለ፥ “ስለ አንተ ዘወትር ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎችም ሆነናል።” ነገር ግን በወደደን በእርሱ ሁሉን ድል እንነሣለን። ነገር ግን ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ አለቆችም ቢሆኑ፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል አምናለሁ። ኀይልም ቢሆን፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ሌላ ፍጥረትም ቢሆን ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል የለም።
ሮሜ 8:19-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል። ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተዳርጓል፤ ይኸውም በራሱ ምርጫ ሳይሆን፣ ለተስፋ እንዲገዛ ካደረገው ከፈቃዱ የተነሣ ነው። ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት እንዲደርስ ነው። እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን። እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ ያገኘን እኛ ራሳችን የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነታችንን በናፍቆት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ተስፋው የሚታይ ከሆነ ግን ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ገና ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፣ በትዕግሥት እንጠብቀዋለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል። ልባችንንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስን ሐሳብ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለቅዱሳን ይማልዳልና። እግዚአብሔር፣ ለሚወድዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውንም ጠራቸው፤ የጠራቸውንም አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም አከበራቸው። ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከርሱ ጋራ እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ እኛ ይማልዳል። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጥረናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
ሮሜ 8:19-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና። እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኵኦንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።
ሮሜ 8:19-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃል። ፍጥረት ሁሉ ከንቱ እንዲሆን ተፈርዶበታል፤ ይኸውም በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በተስፋ እንዲጠባበቅ ባደረገው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ከጥፋት ባርነት ነጻ ወጥቶ ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር የነፃነትና የክብር ተካፋይ እንደሚሆን ነው። ፍጥረት ሁሉ በአንድ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በምጥ ጭንቀት ተይዞ በመቃተት ላይ መኖሩን እናውቃለን። ነገር ግን በመቃተት ላይ ያለው ፍጥረት ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የተቀበልን እኛም የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን የእግዚአብሔር ልጆች መሆንን በተስፋ እየተጠባበቅን በውስጣዊ ሰውነታችን በመቃተት ላይ እንገኛለን፤ እኛ የዳንነው በዚሁ ተስፋ ነው። ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ የሚታየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ነገር ተስፋ ካደረግን ግን በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም እንዴት መጸለይ እንደሚገባን ስለማናውቅ መንፈስ ቅዱስ በድካማችን ይረዳናል፤ በቃል ሊገለጥ በማይቻል መቃተት ያማልደናል። የሰውን ልብ የሚመረምር አምላክ የመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፤ መንፈስ ቅዱስ ስለ ምእመናን የሚያማልደው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እግዚአብሔርን ለሚወዱና እንደ ፈቃዱም ለተጠሩት ሰዎች እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ለበጎ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። ይህም የሆነበት ምክንያት አስቀድሞ ያወቃቸው ልጁን እንዲመስሉና ልጁም ከብዙ ወንድሞች መካከል በኵር እንዲሆን እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ወሰነ ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውንም አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም አከበራቸው። እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል? እግዚአብሔር ለአንድ ልጁ ሳይራራ ስለ እኛ አሳልፎ ከሰጠው እንዴት ከልጁ ጋር ሁሉን ነገር በነጻ አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቃቸው እርሱ ነው። ማነው የሚፈርድ? ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈርድባቸዋልን? እርሱ ስለ እኛ የሞተ፥ ከሞት ተነሥቶ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠ፥ ስለ እኛም የሚማልድ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል ማነው? ችግር ወይስ መከራ? ስደት፥ ወይስ ራብ? ወይስ ራቊትነት፥ ወይስ አደጋ? ወይስ ሰይፍ? ይህም፥ “ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ በወደደን በክርስቶስ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ድል በመንሣት ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ስለዚህ ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ባለሥልጣኖችም ቢሆኑ፥ አሁን ያለውም ቢሆን፥ በኋላ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኀይሎችም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካገኘነው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ።
ሮሜ 8:19-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃልና። ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ ይኸውም በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእርሱ ፈቃድ ነው። ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው የከበረውን ነፃነት እንዲያገኝ ነው። እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ አብሮ በመቃተትና በምጥ ሥቃይ እንደሚኖር እናውቃለንና። ፍጥረት ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን እኛ ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት በናፍቆት እየተጠባበቅን እኛ ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋው የሚታይ ከሆነ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፥ በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ይረዳናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ያማልድልናል፤ ልቦችንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስ ሐሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፥ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ያማልዳልና። እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ዓላማውም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፥ ይህም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው፤ አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህንም ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውን እነዚህንም ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን እነዚህንም ደግሞ አከበራቸው። እንግዲህ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው እርሱ፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው። የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ስለ እኛም በእርግጥ የሚያማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? መከራ ወይስ ሥቃይ፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ረሃብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ አደጋ፥ ወይስ ሰይፍ? ይህም “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህንን ተረድቼአለሁ፤ ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ገዢዎችም ቢሆኑ፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ጥልቀትም ቢሆን፥ ሌላ ፍጥረትም ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።