ወደ ሮም ሰዎች 8:1-18

ወደ ሮም ሰዎች 8:1-18 አማ05

ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖሩ አሁን ኲነኔ የለባቸውም። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ሕይወት የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶኛል። ከሰው ባሕርይ ደካማነት የተነሣ ሕግ ሊያደርገው ያልቻለውን እግዚአብሔር አድርጎታል፤ የገዛ ልጁንም በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌነት በኃጢአት ምክንያት ልኮ በሥጋው ኃጢአትን በፍርድ አስወገደ። ይህንንም ያደረገው በሥጋ ፈቃድ ሳይሆን በመንፈስ ፈቃድ በምንመላለስ በእኛ ትክክለኛው የሕግ ትእዛዝ እንዲፈጸም ነው። በሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሥጋዊ ነገርን፥ በመንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን መንፈሳዊ ነገርን ያስባሉ። ሥጋዊ ነገርን ማሰብ ሞትን ያመጣል፤ መንፈሳዊ ነገርን ማሰብ ግን ሕይወትንና ሰላምን ይሰጣል። ሥጋዊ ነገርን የሚያስብ ሰው ለእግዚአብሔር ሕግ ስለማይታዘዝና መታዘዝም ስለማይችል የእግዚአብሔር ጠላት ነው። ለሥጋዊ ነገር የሚገዙ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ በመንፈስ ፈቃድ እንጂ በሥጋ ፈቃድ አትኖሩም፤ የክርስቶስ መንፈስ የሌለውም ሰው የክርስቶስ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ከሆነ ምንም እንኳ ሥጋችሁ በኃጢአት ምክንያት የሚሞት ቢሆን እግዚአብሔር ስላጸደቃችሁ መንፈሳችሁ ሕያው ነው። ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት ያስነሣው አምላክ በውስጣችሁ በሚኖረው መንፈሱ አማካይነት ለሟች ሥጋችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል። ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! በሕይወታችን ግዴታ አለብን፤ ነገር ግን ይህ ግዴታ በሥጋ ፈቃድ ለመኖር አይደለም። በሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ሥጋዊ ሥራችሁን ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ስለዚህ “አባ! አባታችን ሆይ!” ብላችሁ የምትጠሩበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ በፍርሃት ለመኖር እንደገና የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁም። የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኛ መንፈስ ጋር ሆኖ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለእኛ ይመሰክራል። እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን የእርሱ ወራሾች ነን፤ ከክርስቶስም ጋር እንወርሳለን፤ አሁን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች ብንሆን በኋላ የክብሩ ተካፋዮች እንሆናለን። የአሁኑ ጊዜ መከራ ወደፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ቢመዛዘን በምንም ሊተካከል እንደማይችል አድርጌ እቈጥረዋለሁ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}