መጽሐፈ መዝሙር 138:1-8

መጽሐፈ መዝሙር 138:1-8 አማ05

እግዚአብሔር ሆይ! በሙሉ ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ በመላእክት ፊት ለአንተ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ። ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህና ስለ እውነተኛነትህ የስምህንና የትእዛዞችህን ከፍተኛነት ስላሳየህ ወደ ተቀደሰው ቤተ መቅደስህ እየሰገድኩ ስምህን አመሰግናለሁ። በጠራሁህ ጊዜ ሰማኸኝ፤ በብርታትህም አበረታኸኝ። እግዚአብሔር ሆይ! የቃልህን ተስፋ ስለ ሰሙ የዓለም ነገሥታት ሁሉ ያመሰግኑሃል። ስላደረግኸው ድንቅ ነገር ሁሉና ስለ ታላቅ ክብርህ ይዘምሩልሃል። ከሁሉ በላይ ከፍ ያልክ ሆነህ ሳለ፥ ትሑታንን ትንከባከባለህ፤ ትዕቢተኞችን ግን ከሩቅ ሆነህ ትመለከታቸዋለህ። መከራ ዙሪያዬን በሚከበኝ ጊዜ መከታ ሆነህ በሕይወት ትጠብቀኛለህ፤ በቊጣ የተነሡብኝ ጠላቶቼን ትቃወማቸዋለህ፤ በኀይልህም ትታደገኛለህ። የገባኸውን ቃል ኪዳን ትፈጽምልኛለህ፤ እግዚአብሔር ሆይ! ፍቅርህ ዘለዓለማዊ ነው፤ የእጅህን ሥራ ወደ ፍጻሜ ሳታደርስ አትተወው።