መጽሐፈ ምሳሌ 30:1-33

መጽሐፈ ምሳሌ 30:1-33 አማ05

የማሳ አገር ሰው የያቄ ልጅ አጉር በጥሞና የተናገራቸው ንግግሮች የሚከተሉት ናቸው፦ “አምላክ ሆይ! ደክሜአለሁ፤ አምላክ ሆይ! ደክሜአለሁ፤ እንዴት ልቋቋመው እችላለሁ? ከሰውነት ደረጃ ወጥቼ እንደ እንስሳ ሆኛለሁ፤ ሰው ሊኖረው የሚገባው ማስተዋል የለኝም። ከቶ ጥበብን አልተማርኩም፤ ስለ እግዚአብሔር የማውቀው ምንም ነገር የለኝም። ወደ ሰማይ ወጥቶ የወረደ ማን ነው? ነፋስን በእጁ የጨበጠ፥ ውሃን በልብሱ የቋጠረ፥ የምድርን ዳርቻ ያጸና ማን ነው? የሰውዬው ስም ማነው? የልጁስ ስም ማን ይባላል? ታውቅ እንደሆን ንገረኝ፤ “እግዚአብሔር የሚናገረው ቃል ሁሉ እውነት ነው፤ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻ ነው። እርሱ ያላለውን ብሎአል ብትል ይገሥጽሃል፤ ሐሰተኛ መሆንህንም ይገልጣል።” አምላክ ሆይ! ከመሞቴ በፊት የሚከተሉትን ሁለት ነገሮች እንዳትነሣኝ እለምንሃለሁ፦ ሰውን ከማታለልና ሐሰት ከመናገር ጠብቀኝ፤ የሚያስፈልገኝን ያኽል ምግብ ስጠኝ እንጂ ሀብታም ወይም ድኻ አታድርገኝ። ብዙ ሀብት ቢኖረኝ “እግዚአብሔር ማን ነው?” ብዬ አንተን እስከ መካድ እደርሳለሁ፤ ድኻ ብሆን ደግሞ እሰርቅ ይሆናል፤ በዚህም ሁኔታ የአንተን የአምላኬን ስም አሰድባለሁ። እንዳትረገምና መከራ ላይ እንዳትወድቅ አገልጋይን ባሳዳሪው ፊት አትንቀፈው። አባቶቻቸውን የሚሰድቡ፥ እናቶቻቸውንም የማያመሰግኑ ሰዎች አሉ። በጣም የረከሱ ሆነው ሳለ ንጹሕ የሆኑ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። በትዕቢት የተሞሉና ሰውን የሚንቁ ሰዎች አሉ። ጥርሳቸው እንደ ሰይፍ፥ መንጋጋቸው እንደ ካራ የሆኑ ድኾችንና ችግረኞችን በግፍ የሚበዘብዙ ሰዎች አሉ። አልቅት “ስጠኝ! ስጠኝ!” እያሉ የሚጮኹ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉአት፤ እንዲሁም ከቶ የማይጠግቡና በቃን የማይሉ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ እነርሱም፦ “መቃብር፥ መኻን ሴት፥ ዝናብ የሚያስፈልገው ደረቅ ምድርና ከቊጥጥር ውጪ የሆነ የእሳት ቃጠሎ” ናቸው። በአባቱ የሚያፌዝና እናቱ በምታረጅበት ጊዜ የሚንቃት ሰው የሸለቆ ቊራዎች ዐይኖቹን ጐጥጒጠው ያወጡታል፤ ጆፌ አሞራዎችም ይበሉታል። ላስተውላቸው የማልችል እጅግ ምሥጢር የሆኑ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው። እነርሱም፦ “በሰማይ የሚበር ንስር፥ በአለት ላይ የሚጐተት እባብ፥ በባሕር ላይ የሚጓዝ መርከብና ከሴት ጋር ፍቅር የያዘው ወንድ” ናቸው። የማትታመን ሚስት ሁኔታም እንዲሁ ነው፤ እርስዋ በባልዋ ላይ ታመነዝርና ንጹሕ ሰው በመምሰል “ምንም በደል አልፈጸምኩም” ትላለች። በሦስት ነገሮች ምክንያት ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ ልትታገሥም አትችልም፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ እነርሱም “ባሪያ ሲነግሥ፥ ቦዘኔ ሲጠግብ፥ የተጠላች ሴት ባል ስታገባና፥ ሴት ባሪያ እመቤትዋን ስትወርስ” የሚከሠቱ ሁኔታዎች ናቸው። በዓለም ላይ በብልኅነታቸው የታወቁ አራት ትንንሽ ፍጥረቶች አሉ፤ ጒንዳኖች፦ ጒንዳኖች ደካሞች ናቸው፤ ነገር ግን በበጋ ጊዜ ምግባቸውን ያከማቻሉ። ሽኮኮዎች፦ ሽኮኮዎች ብርቱዎች አይደሉም፤ ነገር ግን መኖሪያቸውን በአለቶች መካከል ይሠራሉ። አንበጦች፦ አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤ ነገር ግን ሁሉም በሥነ ሥርዓት ይጓዛሉ። እንሽላሊቶች፦ እንሽላሊቶች በእጅ ስለሚያዙ ቀላል ፍጥረቶች መስለው ቢታዩም፥ በቤተ መንግሥት እንኳ ሳይቀር በሁሉ ስፍራ ይገኛሉ። አረማመዳቸው አስደሳች የሆነ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ እነርሱም፥ በእንስሶች መካከል ብርቱ የሆኑና ከማንም ፊት የማይሸሹ አንበሶች፥ አውራ ፍየሎች፥ የሚንጐራደዱ አውራ ዶሮዎች፥ በሕዝቦቻቸው ፊት በክብር የሚታዩ ነገሥታት ናቸው። ሞኝነትህ ትምክሕተኛ እንድትሆን ቢያደርግህና ክፉ ነገር ለማድረግ ብታቅድ፥ ቆም ብለህ አስብ። ወተት ቢናጥ ቅቤ ያስገኛል፤ የሰው አፍንጫ ቢጠመዘዝ ይደማል፤ ቊጣ ቢነሣሣ ጠብን ያመጣል።