ምሳሌ 30:1-33

ምሳሌ 30:1-33 NASV

የያቄ ልጅ የአጉር ቃል ይህ ነው፤ ይህ ሰው ለኢቲኤል፣ ለኢቲኤልና ለኡካል ተናገረ፤ “እኔ ከሰው ሁሉ ይልቅ ደነዝ ነኝ፤ ሰው ያለው ማስተዋል የለኝም። ጥበብን አልተማርሁም፤ ስለ ቅዱሱም ዕውቀት የለኝም። ወደ ሰማይ የወጣ፣ የወረደስ ማነው? ነፋስን በእጁ ሰብስቦ የያዘ ማነው? ውሆችንስ በመጐናጸፊያው የጠቀለለ ማነው? የምድርን ዳርቻዎች ሁሉ የወሰነ ማነው? ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ይባላል? የምታውቅ ከሆነ እስኪ ንገረኝ! “የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ እርሱ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻቸው ነው። በርሱ ቃል ላይ አንዳች አትጨምር፤ አለዚያ ይዘልፍሃል፤ ሐሰተኛም ያደርግሃል። “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሁለት ነገር እለምንሃለሁ፤ እነዚህንም ከመሞቴ በፊት አትከልክለኝ፤ ሐሰትንና ሐሰት መናገርን ከእኔ አርቅልኝ፤ ድኽነትንም ሆነ ብልጽግናን አትስጠኝ፤ ብቻ የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ። አለዚያ ግን ያለ ልክ እጠግብና እክድሃለሁ፤ ‘እግዚአብሔር ማን ነው?’ እላለሁ፤ ወይም ድኻ እሆንና እሰርቃለሁ፤ የአምላኬንም ስም አሰድባለሁ። “አገልጋይን በጌታው ፊት በክፉ አታንሣው፤ አለዚያ ይረግምህና ጕዳት ያገኝሃል። “አባቱን የሚረግም፣ እናቱን የማይባርክ ትውልድ አለ፤ ራሳቸውን ንጹሓን አድርገው የሚቈጥሩ፣ ሆኖም ከርኩሰታቸው ያልነጹ አሉ፤ ዐይናቸው ትዕቢተኛ የሆነ፣ አስተያያቸው ንቀት የሞላበት፣ ድኾችን ከምድር፣ ችግረኞችንም ከሰው ዘር መካከል ለማጥፋት፣ ጥርሳቸው ሰይፍ የሆነ፣ መንጋጋቸውም ካራ የሆነ አሉ። “አልቅት ሁለት ሴት ልጆች አሉት፤ ‘ስጡን! ስጡን!’ እያሉ ይጮኻሉ። “ፈጽሞ የማይጠግቡ ሦስት ነገሮች አሉ፤ ‘በቃኝን’ ከቶ የማያውቁ አራት ናቸው፤ እነርሱም መቃብር፣ መካን ማሕፀን፣ ውሃ ጠጥታ የማትረካ ምድር፣ ‘በቃኝ’ የማይል እሳት ናቸው። “በአባት ላይ የምታፌዝ ዐይን፣ የእናትንም ትእዛዝ የምትንቅ፣ የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጧታል፤ ጆፌ አሞሮችም ይበሏታል። “እጅግ የሚያስደንቁኝ ሦስት ነገሮች አሉ፤ የማላስተውላቸውም አራት ናቸው፤ የንስር መንገድ በሰማይ፣ የእባብ መንገድ በቋጥኝ፣ የመርከብ መንገድ በባሕር፣ የሰውም መንገድ ከሴት ልጅ ጋራ ናቸው። “የአመንዝራዪቱ መንገድ ይህ ነው፤ በልታ አፏን በማበስ፣ ‘ምንም የሠራሁት ጥፋት የለም’ ትላለች። “ምድር በሦስት ነገር ትናወጣለች፤ እንዲያውም መሸከም የማትችላቸው አራት ነገሮች ናቸው፤ ባሪያ ሲነግሥ፣ ሰነፍ እንጀራ ሲጠግብ፣ የተጠላች ሴት ባል ስታገባ፣ ሴት ባሪያ በእመቤቷ እግር ስትተካ። “በምድር ላይ አራት ነገሮች ትንንሽ ናቸው፤ ሆኖም እጅግ ጠቢባን ናቸው፤ ጕንዳኖች ደካማ ፍጥረታት ናቸው፤ ሆኖም ምግባቸውን በበጋ ያከማቻሉ። ሽኮኮዎች ዐቅመ ደካማ ናቸው፤ ሆኖም መኖሪያቸውን በቋጥኞች መካከል ይሠራሉ፤ አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤ ሆኖም ቅደም ተከተል ይዘው ይጓዛሉ፤ እንሽላሊት በእጅ ትያዛለች፤ ሆኖም በቤተ መንግሥት ትገኛለች። “አረማመዳቸው ግርማዊ የሆነ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም በሞገስ የሚጐማለሉ አራት ናቸው፤ ከአራዊት መካከል ኀይለኛ የሆነው፣ ከምንም ነገር ፊት ግንባሩን የማያጥፈው አንበሳ፤ ጐርደድ ጐርደድ የሚል አውራ ዶሮ፣ አውራ ፍየል፣ እንዲሁም በሰራዊቱ የታጀበ ንጉሥ ናቸው። “ተላላ ሆነህ ራስህን ከፍ ከፍ ካደረግህ፣ ወይም ክፉ ነገር ካቀድህ፣ እጅህን በአፍህ ላይ አድርግ። ወተት ሲናጥ ቅቤ እንደሚወጣው፣ አፍንጫን ሲያሹት እንደሚደማ፣ ቍጣን ማነሣሣትም ጥልን ይፈጥራል።”