ሀብታም ሆኖ በሁከት ከመኖር ድኻ ሆኖ እግዚአብሔርን በማክበር መኖር ይሻላል። ጥላቻ ባለበት ስፍራ ጮማ ሥጋ ከመብላት ፍቅር ባለበት ስፍራ ጎመን መብላት ይሻላል። ቊጣ ጭቅጭቅን ያነሣሣል፤ ትዕግሥት ግን ጠብን ያበርዳል። የሰነፍ መንገድ በችግር እሾኽ የታጠረ ነው፤ የቅን ሰው መንገድ ግን እንደ ተስተካከለ ጐዳና ነው። ብልኅ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሞኝ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል። ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች በሞኝነታቸው ይደሰታሉ፤ ብልኆች ግን ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋሉ። መልካም ምክርን ብትቀበል ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ ምክርን ባትቀበል ግን ምንም ነገር አይሳካልህም። ተገቢውን ቃል በተገቢው ቦታ መናገር እጅግ ያስደስታል። ብልኾች ወደ ላይ በሚያመራው በሕይወት መንገድ ይሄዳሉ እንጂ፥ ወደ ታች በሚያወርደው በሞት መንገድ አይሄዱም። እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ቤት ይደመስሳል፤ ባልዋ የሞተባትን ሴት ድንበር እንዳይገፋ ይጠብቃል። እግዚአብሔር ክፉ ሐሳብን ይጠላል፤ ንጹሕ በሆነ ቃል ግን ደስ ይለዋል። በማጭበርበር ትርፍ ለማግኘት ብትሞክር ቤተሰብህን በችግር ላይ ትጥላለህ፤ ጉቦ አትቀበል፤ ለረጅም ዘመንም ትኖራለህ። ደጋግ ሰዎች ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ፤ ክፉዎች ግን በችኰላ ክፉ ቃል ይናገራሉ። እግዚአብሔር ከክፉዎች የራቀ ነው፤ ደጋግ ሰዎች ሲጸልዩ ግን ይሰማቸዋል። በፈገግታ የተሞላ ፊት ልብን ያስደስታል፤ የምሥራች ቃልም አጥንትን ያለመልማል። ሕይወት የሚሰጥ ምክር የሚቀበል የጠቢባን ጓደኛ ይሆናል። ተግሣጽን የሚጠላ ራሱን ይጐዳል። ተግሣጽን የሚቀበል ግን ጥበብን ይጨምራል። እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን የሚሰጥ ትምህርት ነው፤ ክብርን ለማግኘት በቅድሚያ ትሑት መሆን ያስፈልጋል።
መጽሐፈ ምሳሌ 15 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ምሳሌ 15:16-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች