መጽሐፈ ምሳሌ 14:1-18

መጽሐፈ ምሳሌ 14:1-18 አማ05

ጥበበኛ ሴት ቤትዋን በሥነ ሥርዓት ታስተዳድራለች፤ ሞኝ ሴት ግን በገዛ እጅዋ ታፈርሰዋለች። አካሄዱ ቀጥተኛ የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ሰው ግን እግዚአብሔርን አይፈራም። ሞኝን የገዛ ንግግሩ ያስቀጣዋል፤ ጥበበኞችን ግን መልካም አነጋገራቸው ይጠብቃቸዋል። የምታርስባቸው በሬዎች ከሌሉህ ጐተራህ ባዶ ይሆናል። በሬዎች ካሉህ ግን ጐተራህ በእህል የተሞላ ይሆናል። ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን የሚናገረው ሐሰት ነው። ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል፤ አያገኛትም። አስተዋዮች ግን ዕውቀትን በቀላሉ ይገበያሉ። ከእነርሱ የምትማረው ምንም ዕውቀት ስለሌለ ከሞኞች ራቅ። የብልኅ ሰው ጥበብ መንገዱን እንዳይስት ያደርገዋል። ሞኝን ሰው ግን ሞኝነቱ መንገዱን እንዲስት ያደርገዋል። ሞኞች ኃጢአት ሲሠሩ በመጸጸት ፈንታ ያፌዛሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው ይፈልጋሉ። ደስታህም ሆነ ሐዘንህ የራስህ ነው፤ ማንም የሚካፈልህ የለም። የክፉ ሰው ቤት ይፈርሳል፤ የደግ ሰው ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። አንተ “ትክክለኛ መንገድ ነው” ብለህ የምታስበው ወደ ሞት ይመራህ ይሆናል። በሳቅ ጊዜ እንኳ በልብ ውስጥ ሐዘን ሊኖር ይችላል፤ የደስታም ፍጻሜ ለቅሶ ነው። ከሐዲዎች ሰዎች የክፉ ሥራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ። ሞኝ ሰው የሚነግሩትን ሁሉ አምኖ ይቀበላል፤ ብልኆች ግን እርምጃቸውን በጥንቃቄ ይመረምራሉ። ብልኆች እግዚአብሔርን ስለሚፈሩ ከክፉ ነገር ለመራቅ ይጠነቀቃሉ፤ ሞኞች ግን ከአደጋ የማይጠነቀቁ ችኲሎች ናቸው። ቊጡ ሰው የሞኝነትን ሥራ ይሠራል፤ ጥበበኛ ግን ይታገሣል። አላዋቂዎች የስንፍናቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ ብልኆች ግን ዕውቀትን እንደ አክሊል ይቀዳጃሉ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}