ምሳሌ 14:1-18

ምሳሌ 14:1-18 NASV

ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ ቂል ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች። አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ይንቀዋል። የቂል ሰው ንግግር ለጀርባው በትር ታስከትልበታለች፤ የጥበበኛ ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። በሬዎች በሌሉበት በረቱ ባዶ ይሆናል፤ በበሬ ጕልበት ግን ብዙ ምርት ይገኛል። ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይዘከዝካል። ፌዘኛ ጥበብን ይሻል፤ ሆኖም አያገኛትም፤ ዕውቀት ግን ለአስተዋዮች በቀላሉ ትገኛለች። ከሞኝ ሰው ራቅ፣ ከከንፈሮቹ ዕውቀት አታገኝምና። የአስተዋዮች ጥበብ መንገዳቸውን ልብ ማለት ነው፤ የሞኞች ቂልነት ግን መታለል ነው። ቂሎች በሚያቀርቡት የበደል ካሳ ያፌዛሉ፤ በቅኖች መካከል ግን በጎ ፈቃድ ትገኛለች። እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል፤ ደስታውንም ማንም ሊጋራው አይችልም። የክፉዎች ቤት ይፈርሳል፤ የቅኖች ድንኳን ግን ይስፋፋል። ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል። በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል፤ ደስታም በሐዘን ሊፈጸም ይችላል። ልባቸውን ከጽድቅ የሚመልሱ የእጃቸውን ሙሉ ዋጋ ይቀበላሉ፤ ደግ ሰውም ወሮታውን ያገኛል። አላዋቂው ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል። ጠቢብ ሰው ጥንቁቅ ነው፤ ከክፉም ይርቃል፤ ሞኝ ግን ችኵልና ደንታ ቢስ ነው። ግልፍተኛ ሰው የቂል ተግባር ይፈጽማል፤ መሠሪም ሰው አይወደድም። አላዋቂዎች ቂልነትን ይወርሳሉ፤ አስተዋዮች ግን ዕውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}