ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:9-18

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:9-18 አማ05

በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው። ስለዚህ ለኢየሱስ ስም ክብር፥ በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችም ያሉት ሁሉ በጒልበታቸው ይንበረከካሉ። በአንደበታቸውም “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው በመመስከር ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ። ወዳጆቼ ሆይ! እኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ሁልጊዜ ታዛዦች እንደ ነበራችሁ፥ ይልቁንም አሁን ከእናንተ በራቅሁበት ጊዜ ይበልጥ ታዛዦች እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፤ ስለዚህ እያንዳንዳችሁ መዳናችሁን ፍጹም ለማድረግ በፍርሃትና በአክብሮት ተግታችሁ ሥሩ። እግዚአብሔር ታዛዥነትን ለእናንተ እየሰጠ ዓላማውን ከፍጻሜ ለማድረስ በእናንተ ውስጥ ይሠራል። ማናቸውንም ሥራ በምትሠሩበት ጊዜ አታጒረምርሙ ወይም አትከራከሩ። ይህም ከሆነ በዚህ በጠማማና በመጥፎ ትውልድ መካከል ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ንጹሓን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት ታበራላችሁ። ይህም የሚሆነው ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ሳታቋርጡ አጥብቃችሁ በመያዝ ነው፤ በዚህ ዐይነት ሩጫዬም ሆነ ሥራዬ ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የምመካበት ምክንያት ይኖረኛል ማለት ነው። ለእግዚአብሔር በእምነት በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ የእኔም ሕይወት ተጨማሪ መሥዋዕት ሆኖ ቢቀርብ እንኳ ደስ ይለኛል፤ እናንተም የደስታዬ ተካፋዮች ትሆናላችሁ። እንዲሁም እናንተ ተደስታችሁ እኔንም የደስታችሁ ተካፋይ ታደርጉኛላችሁ።