ፊልጵስዩስ 2:9-18
ፊልጵስዩስ 2:9-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህም እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምንም ሰጠው። ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና ከምድር በታች ያለ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው። አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ ነው። አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ ዘወትር እንደምትሰሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፥ ሳልኖርም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ሆናችሁ ለድኅነታችሁ ሥሩ። ለሚወደው ሥራ የሚረዳችሁ እርሱ እግዚአብሔር ይቅርታውን ይፈጽምላችሁ። የምትሠሩትን ሁሉ ያለ ማንጐራጐርና ያለ መጠራጠር በፍቅርና በስምምነት ሥሩ። እንደ እግዚአብሔር ልጆች ንጹሓንና የዋሃን ትሆኑ ዘንድ፥ በማያምኑና በጠማሞች ልጆች መካከል ነውር ሳይኖርባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፤ የሕይወትን ቃል እያስተማራችሁ፤ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን እኔ እንድመካ፤ የሮጥሁ በከንቱ አይደለምና፤ የደከምሁም በከንቱ አይደለምና። ስለ ሃይማኖታችሁም የአምልኮ መሥዋዕትን እሠዋለሁ። እነሆም እኔ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ እናንተም በእኔ ደስ ይበላችሁ። ከእኔም ጋር ሐሤት አድርጉ።
ፊልጵስዩስ 2:9-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው። የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቍርባን ብፈስስ እንኳ ከሁላችሁ ጋራ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ። እናንተም እንደዚሁ ከእኔ ጋራ ደስ ልትሠኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል።
ፊልጵስዩስ 2:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ።
ፊልጵስዩስ 2:9-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው። ስለዚህ ለኢየሱስ ስም ክብር፥ በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችም ያሉት ሁሉ በጒልበታቸው ይንበረከካሉ። በአንደበታቸውም “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው በመመስከር ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ። ወዳጆቼ ሆይ! እኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ሁልጊዜ ታዛዦች እንደ ነበራችሁ፥ ይልቁንም አሁን ከእናንተ በራቅሁበት ጊዜ ይበልጥ ታዛዦች እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፤ ስለዚህ እያንዳንዳችሁ መዳናችሁን ፍጹም ለማድረግ በፍርሃትና በአክብሮት ተግታችሁ ሥሩ። እግዚአብሔር ታዛዥነትን ለእናንተ እየሰጠ ዓላማውን ከፍጻሜ ለማድረስ በእናንተ ውስጥ ይሠራል። ማናቸውንም ሥራ በምትሠሩበት ጊዜ አታጒረምርሙ ወይም አትከራከሩ። ይህም ከሆነ በዚህ በጠማማና በመጥፎ ትውልድ መካከል ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ንጹሓን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት ታበራላችሁ። ይህም የሚሆነው ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ሳታቋርጡ አጥብቃችሁ በመያዝ ነው፤ በዚህ ዐይነት ሩጫዬም ሆነ ሥራዬ ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የምመካበት ምክንያት ይኖረኛል ማለት ነው። ለእግዚአብሔር በእምነት በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ የእኔም ሕይወት ተጨማሪ መሥዋዕት ሆኖ ቢቀርብ እንኳ ደስ ይለኛል፤ እናንተም የደስታዬ ተካፋዮች ትሆናላችሁ። እንዲሁም እናንተ ተደስታችሁ እኔንም የደስታችሁ ተካፋይ ታደርጉኛላችሁ።
ፊልጵስዩስ 2:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ የሚበልጠውን ስም ሰጠው፤ በዚህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም እንዲንበረከኩና መላስ ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር እንዲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ እንዲመሰክሩ ነው። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ ይበልጥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ በጎ ፈቃዱን እንድትፈልጉና እንድታደርጉ ሁለቱንም በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ሁሉንም ነገሮች ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ በዚህም በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ሆናችሁ በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት የምታበሩ፥ ያለ ነቀፋ የዋሆችና ነውርም የሌለባችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ትሆናላችሁ፤ እናንተም የሕይወትን ቃል በጽኑ በመያዛችሁ ምክንያት በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ነገር ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቊርባን ብፈስስ ደስ ይለኛል፤ ከእናንተም ከሁላችሁ ጋር አብሬ ሐሤት አደርጋለሁ፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ፤ ከእኔም ጋር አብራችሁ ሐሤት አድርጉ።