ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:1-30

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:1-30 አማ05

በክርስቶስ መበረታታት ካላችሁ፥ በፍቅሩም የተጽናናችሁ ከሆነ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ኅብረት ካላችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግነትንና ርኅራኄን ካሳያችሁ፥ ስለዚህ በሐሳብ፥ በፍቅር፥ በመንፈስ፥ በዓላማ እየተስማማችሁ ደስታዬ የተሟላ እንዲሆን አድርጉ። በትሕትና ተሞልታችሁ ሌሎች ሰዎች ከእናንተ እንደሚሻሉ አድርጋችሁ ቊጠሩ እንጂ በራስ ወዳድነት ወይም “ያለ እኔ ማን አለ” በሚል ትምክሕት ምንም ነገር አታድርጉ። እንዲሁም እያንዳንዱ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በዚህ ዐይነት ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየው የትሕትና ሥራ በእናንተም ሕይወት ሊኖር ይገባል። እርሱ ሁልጊዜ የመለኮት ባሕርይ አለው። ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሚያደርገውን የመለኮት ባሕርይ በኃይል እንደ ያዘ አልቈጠረውም። ይልቁንም ያለውን ክብር ሁሉ ትቶ እንደ ባሪያ ሆኖ ታየ እንደ ሰውም ተወለደ፤ በሰው አምሳልም ተገለጠ፤ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት ድረስ፥ ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው። ስለዚህ ለኢየሱስ ስም ክብር፥ በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችም ያሉት ሁሉ በጒልበታቸው ይንበረከካሉ። በአንደበታቸውም “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው በመመስከር ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ። ወዳጆቼ ሆይ! እኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ሁልጊዜ ታዛዦች እንደ ነበራችሁ፥ ይልቁንም አሁን ከእናንተ በራቅሁበት ጊዜ ይበልጥ ታዛዦች እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፤ ስለዚህ እያንዳንዳችሁ መዳናችሁን ፍጹም ለማድረግ በፍርሃትና በአክብሮት ተግታችሁ ሥሩ። እግዚአብሔር ታዛዥነትን ለእናንተ እየሰጠ ዓላማውን ከፍጻሜ ለማድረስ በእናንተ ውስጥ ይሠራል። ማናቸውንም ሥራ በምትሠሩበት ጊዜ አታጒረምርሙ ወይም አትከራከሩ። ይህም ከሆነ በዚህ በጠማማና በመጥፎ ትውልድ መካከል ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ንጹሓን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት ታበራላችሁ። ይህም የሚሆነው ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ሳታቋርጡ አጥብቃችሁ በመያዝ ነው፤ በዚህ ዐይነት ሩጫዬም ሆነ ሥራዬ ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የምመካበት ምክንያት ይኖረኛል ማለት ነው። ለእግዚአብሔር በእምነት በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ የእኔም ሕይወት ተጨማሪ መሥዋዕት ሆኖ ቢቀርብ እንኳ ደስ ይለኛል፤ እናንተም የደስታዬ ተካፋዮች ትሆናላችሁ። እንዲሁም እናንተ ተደስታችሁ እኔንም የደስታችሁ ተካፋይ ታደርጉኛላችሁ። እኔ ስለ እናንተ ሁኔታ በመስማት እንድጽናና ጢሞቴዎስን በፍጥነት ወደ እናንተ ለመላክ እንደሚያስችለኝ በጌታ ኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለ እናንተ ሁኔታ ከልብ የሚያስብ ከጢሞቴዎስ በቀር ሌላ ሰው የለኝም። ሌሎቹ ግን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ያሳድዳሉ እንጂ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ግድ የላቸውም። ጢሞቴዎስ፥ ታማኝነቱ ተፈትኖ የተመሰከረለት መሆኑንና ከእኔም ጋር እንደ አባትና ልጅ ተባብረን ወንጌልን በማስተማር አብረን ስንሠራ መቈየታችንን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። ስለዚህ የእኔ ጉዳይ ከምን እንደሚደርስ ከተረዳሁ በኋላ ጢሞቴዎስን በፍጥነት ወደ እናንተ እንደምልክላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። እንዲያውም እኔ ራሴ በቶሎ ወደ እናንተ መምጣት እንድችል ጌታ ይረዳኛል ብዬ እተማመናለሁ። እንዲሁም እኔን በሚያስፈልገኝ ሁሉ እንዲረዳኝ ልካችሁት የነበረውን ወንድሜን ኤጳፍሮዲቱስን ወደ እናንተ መላክ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ እርሱ ከእኔ ጋር የተሰለፈ ወታደርና የሥራ ጓደኛዬ ሆኖ ሲሠራ የቈየ ነው። እርሱን ወደ እናንተ የምልከውም ሁላችሁንም ለማየት በመናፈቁና እናንተም መታመሙን በመስማታችሁ ስለ ተጨነቀ ነው። በእርግጥ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ምሕረት አደረገለት፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ሐዘን በሐዘን ላይ እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ጭምር ምሕረት አደረገ። ስለዚህ እናንተ እርሱን በማየት እንድትደሰቱና የእኔም ሐዘን እንዲቃለል እርሱን ወደ እናንተ ልልከው በይበልጥ ፈለግኹ። እንግዲህ በጌታ አማኝ እንደ መሆኑ በደስታ ተቀበሉት፤ እንደ እርሱ ያሉትንም ሰዎች ሁሉ አክብሩአቸው። እናንተ በቅርብ ተገኝታችሁ ልታደርጉልኝ ያልቻላችሁትን ርዳታ እርሱ ለማሟላት ብሎ ስለ ክርስቶስ ሥራ ለሕይወቱ ሳይሳሳ ለሞት ተቃርቦ ነበር።