ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል። ሌላው የምደሰትበት ምክንያት በእናንተ ጸሎትና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ርዳታ ነጻ እንደምወጣ ስለማውቅ ነው። በፍጹም እንደማላፍር በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን ዘወትር እንደማደርገውና ዛሬ በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት ክርስቶስ በሰውነቴ ይከብራል ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። ስለዚህ ለእኔ ሕይወት ማለት በክርስቶስ መኖር ነው፤ ሞትም ማለት ጥቅም የሚገኝበት ነገር ነው። ይሁን እንጂ በዚሁ ሥጋዊ አካሌ ቀጥዬ የምኖር ብሆን ፍሬ የሚሰጥ ሥራ መሥራት ማለት ነው፤ ሆኖም ግን ቀጥዬ ከመኖርና ከመሞት የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ተይዤአለሁ፤ በአንድ በኩል ከክርስቶስ ጋር መሆን ከሁሉ የሚበልጥ ነገር ስለ ሆነ ከዚህ ሕይወት ተለይቼ ከክርስቶስ ጋር መሆንን እፈልጋለሁ ይኸውም ከክርስቶስ ጋር መኖር እጅግ የተሻለ ስለ ሆነ ነው። በሌላ በኩል በሕይወት መኖሬ ለእናንተ የበለጠ አስፈላጊ ነው። በዚህ በመተማመን እኔ ከሞት ተርፌ እምነታችሁ እንዲያድግና ደስታን እንድታገኙ ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ ዐውቃለሁ። እኔም እንደገና ወደ እናንተ ስመጣ በእኔ ምክንያት ያላችሁ ትምክሕት በኢየሱስ ክርስቶስ ይበዛል። እንግዲህ ከሁሉም በላይ ሕይወታችሁ የክርስቶስን ወንጌል የሚያስመሰግን ይሁን፤ ይህም እኔ መጥቼ ባያችሁም ወይም ከእናንተ ብርቅ በአንድ ዓላማ ጸንታችሁ መቆማችሁንና ወንጌልን በኅብረት ለማዳረስ መጋደላችሁን እሰማለሁ። ተቃዋሚዎቻችሁንም በምንም ነገር አትፍሩአቸው፤ ይህም ድፍረታችሁ ለእነርሱ የመጥፋታቸው ምልክት ሲሆን ለእናንተ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ የመዳኛችሁ ምልክት ነው። ክርስቶስን የማገልገል ዕድል የተሰጣችሁ በእርሱ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ምክንያት መከራ እንድትቀበሉም ጭምር ነው። ስለዚህ አሁን ከእኔ ጋር የመከራ ተካፋዮች ሆናችኋል፤ ይህም መከራ ከዚህ በፊት ደርሶብኝ ያያችሁትና አሁንም እየደረሰብኝ መሆኑን የምትሰሙት ነው።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1:18-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች