የማቴዎስ ወንጌል 24:3-14

የማቴዎስ ወንጌል 24:3-14 አማ05

ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ይህ ሁሉ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? የመምጫህና የዘመኑ መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም ሰው እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ። የጦርነትን ድምፅና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ ይህ ሁሉ መሆን ስላለበት አትደንግጡ፤ መጨረሻው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ በጦርነት ይነሣል፤ በልዩ ልዩ ስፍራ ራብና የምድር መናወጥ ይሆናል። ይህም ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋል፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ሃይማኖታቸውን በመካድ ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤ ከክፋት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል በመላው ዓለም ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች