የማቴዎስ ወንጌል 21:8-22
የማቴዎስ ወንጌል 21:8-22 አማ05
ከሕዝቡም ብዙዎቹ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቀጠፉ በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር። ከሕዝቡም ፊት ለፊት ይሄዱ የነበሩትና ከኋላ ይከተሉ የነበሩት፥ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ምስጋና ይሁን! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሳዕና! ምስጋና በአርያም ለእግዚአብሔር ይሁን!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ የከተማው ሰዎች በሙሉ “ይህ ማን ነው?” በማለት ታወኩ። ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ምድር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዚያም የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ሁሉ አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ። “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሳለ ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስ ያደረገውን ድንቅ ነገር በማየታቸውና ሕፃናትም በቤተ መቅደስ “ለዳዊት ልጅ ሆሳዕና! ምስጋና ይሁን!” እያሉ ሲጮኹ በመስማታቸው ተቈጡ። ስለዚህ ኢየሱስን “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት፤ እርሱም “አዎ፥ እሰማለሁ፤ ‘ከልጆችና ከሚጠቡት ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው፤ ትቶአቸውም ከከተማ ወጥቶ ቢታንያ ወደምትባል መንደር ሄደ፤ በዚያም ዐደረ። ኢየሱስ ጠዋት በማለዳ፥ ወደ ከተማ ተመልሶ ሲሄድ ራበው፤ አንዲት የበለስ ዛፍ በመንገድ ዳር አየና ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ “ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ፍሬ አይገኝብሽ!” አላት። ዛፊቱም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ይህች የበለስ ዛፍ በአንድ አፍታ እንዴት ደረቀች!” በማለት ተገረሙ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁና ባትጠራጠሩ በበለሲቱ ዛፍ ላይ እንደ ተደረገው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህንን ተራራ እንኳ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር!’ ብትሉት ይሆንላችኋል። አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።”

