ማቴዎስ 21:8-22
ማቴዎስ 21:8-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቍኦረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሣዕና በአርያም!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ “ይህ ማን ነው?” ብሎ ተናወጠ። ሕዝቡም “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው፤” አሉ። ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት፤” አላቸው። በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ!” እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” አሉት። ኢየሱስም “እሰማለሁ፤ ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ፤’ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ፤ በዚያም አደረ። በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና “ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ፤” አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው “በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች?” ብለው ተደነቁ። ኢየሱስም መልሶ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር፤’ ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ፤” አላቸው።
ማቴዎስ 21:8-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከሕዝቡም አብዛኛው ልብሶቻቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎቹም ከዛፎች ቅርንጫፍ እየዘነጠፉ በመንገዱ ላይ ያነጥፉ ነበር። ቀድሞት የሚሄደውና ይከተለው የነበረው ሕዝብም እንዲህ እያለ ይጮኽ ነበር፤ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ!” “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!” “ሆሳዕና በአርያም!” ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፣ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች። ሕዝቡም፣ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ በመገለባበጥ፣ “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን፣ ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሳዕና፤ ለዳዊት ልጅ” እያሉ በመቅደስ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ። እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን? “ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣ ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ” ትቷቸው ከከተማው ወጣ፤ ወደ ቢታንያም ሄዶ በዚያው ዐደረ። ኢየሱስ በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማዪቱ በመመለስ ላይ ሳለ ተራበ፤ በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሲሄድ ከቅጠል በቀር ምንም ስላላገኘባት፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ፍሬ አይኑርብሽ!” አላት፤ የበለሷም ዛፍ ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም የሆነውን አይተው በመደነቅ፣ “የበለሷ ዛፍ እንዴት በአንዴ ልትደርቅ ቻለች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩ፣ በበለሷ ዛፍ ላይ የሆነውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።”
ማቴዎስ 21:8-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቍኦረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ፦ ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ። ሕዝቡም፦ ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው አሉ። ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና፦ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቍኦጥተው፦ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረ። በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና፦ ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው፦ በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው።
ማቴዎስ 21:8-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከሕዝቡም ብዙዎቹ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቀጠፉ በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር። ከሕዝቡም ፊት ለፊት ይሄዱ የነበሩትና ከኋላ ይከተሉ የነበሩት፥ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ምስጋና ይሁን! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሳዕና! ምስጋና በአርያም ለእግዚአብሔር ይሁን!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ የከተማው ሰዎች በሙሉ “ይህ ማን ነው?” በማለት ታወኩ። ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ምድር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዚያም የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ሁሉ አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ። “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሳለ ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስ ያደረገውን ድንቅ ነገር በማየታቸውና ሕፃናትም በቤተ መቅደስ “ለዳዊት ልጅ ሆሳዕና! ምስጋና ይሁን!” እያሉ ሲጮኹ በመስማታቸው ተቈጡ። ስለዚህ ኢየሱስን “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት፤ እርሱም “አዎ፥ እሰማለሁ፤ ‘ከልጆችና ከሚጠቡት ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው፤ ትቶአቸውም ከከተማ ወጥቶ ቢታንያ ወደምትባል መንደር ሄደ፤ በዚያም ዐደረ። ኢየሱስ ጠዋት በማለዳ፥ ወደ ከተማ ተመልሶ ሲሄድ ራበው፤ አንዲት የበለስ ዛፍ በመንገድ ዳር አየና ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ “ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ፍሬ አይገኝብሽ!” አላት። ዛፊቱም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ይህች የበለስ ዛፍ በአንድ አፍታ እንዴት ደረቀች!” በማለት ተገረሙ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁና ባትጠራጠሩ በበለሲቱ ዛፍ ላይ እንደ ተደረገው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህንን ተራራ እንኳ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር!’ ብትሉት ይሆንላችኋል። አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።”
ማቴዎስ 21:8-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እጅግ ብዙ ሕዝብም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። ከፊቱ ይሄዱ የነበሩትና ይከተሉት የነበሩት ሕዝብ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሣዕና በአርያም!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ “ይህ ማን ነው?” ብሎ መላው ከተማ ተናወጠ። ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን ወንበሮች ገለበጠ፤ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው። በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ነገር ግን ሊቃነ ካህናትና ጻፎች ያደረገውን ድንቅ ነገርና በመቅደስም “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ!” እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቆጡ፤ “እነዚህ የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት። ኢየሱስም “አዎን እሰማለሁ፤ ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። ትቶአቸውም ከከተማ ወጥቶ ወደ ቢታንያ ሄደ፤ በዚያም አደረ። በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ራበው። በመንገድ ዳር የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን ከቅጠል በስተቀር ምንም አላገኘባትም፤ “እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይገኝብሽ” አላት። የበለስዋ ዛፍም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህንን አይተው በመደነቅ “የበለስዋ ዛፍ ወዲያውኑ እንዴት ደረቀች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ፥ በበለሲቱ ዛፍ እንደተደረገው ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ትቀበላላችሁ።”