የሉቃስ ወንጌል 21:1-9
የሉቃስ ወንጌል 21:1-9 አማ05
ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች መባቸውን በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ውስጥ ሲጨምሩ አየ። እንዲሁም አንዲት ድኻ መበለት፥ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በሣጥኑ ውስጥ ስትጨምር አየ። እንዲህም አለ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት፥ ከሁሉም አብልጣ ሰጥታለች። እነርሱ የሰጡት ከሀብታቸው የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።” አንዳንድ ሰዎች፥ “ይህ ቤተ መቅደስ እንዴት ውብ ነው? በከበሩ ድንጋዮችና ለእግዚአብሔር በቀረቡ ስጦታዎች አጊጦአል” እያሉ ይነጋገሩ ነበር። ኢየሱስ ግን “ይህ የምታዩት ሁሉ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል፤ እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ አንድ ቀን ይፈራርሳሉ።” እነርሱም “መምህር ሆይ! ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡን የምናውቅበት ምልክት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ! እነሆ፥ ጊዜው ቀርቦአል!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እነርሱን አትከተሉአቸው። ስለ ጦርነትና ስለ ሁከት በምትሰሙበት ጊዜም አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ይሁን እንጂ ፍጻሜው ወዲያውኑ አይሆንም።”

