ሰቈቃወ ኤርምያስ 2:5-19

ሰቈቃወ ኤርምያስ 2:5-19 አማ05

እግዚአብሔር እንደ ጠላት እስራኤልን አጠፋ፤ ቤተ መንግሥቶችዋን አወደመ፤ ምሽጎችዋን አፈራረሰ፤ በይሁዳ ሕዝብም ለቅሶና ዋይታን አበዛ። መቅደሱን በአትክልት ቦታ ውስጥ እንዳለ መጠለያ አወደመ፤ እግዚአብሔር በጽዮን በዓሎችንና ሰንበቶችን አስቀረ፤ በኀይለኛ ቊጣውም ንጉሡንና ካህኑን አዋረደ። እግዚአብሔር መሠዊያውን ናቀ፤ መቅደሱንም ተወ፤ የቤተ መንግሥቶችዋን ቅጽሮች ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤ በበዓላት ቀን እንደሚደረገው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከፍተኛ ድምፅ ተሰማ። እግዚአብሔር የኢየሩሳሌምን ከተማ ቅጽር ለማፍረስ ወስኖ ገመዱን ዘረጋ፤ ከማጥፋት አልተመለሰም፤ የመጠበቂያ ግንቡና ቅጽሩ ተፈረካከሱ፤ በአንድነትም ፈረሱ። የቅጽር በሮች ከመሬት በታች ተቀበሩ፤ መወርወሪያዎቻቸውም ተሰባብረው ወደቁ፤ ንጉሡና መሳፍንቱ አሁን በአሕዛብ መካከል በስደት ላይ ናቸው፤ የኦሪት ሕግ ትምህርት ከእንግዲህ ወዲህ አይሰጥም፤ ነቢያትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አይገለጥላቸውም። የኢየሩሳሌም ከተማ ሽማግሌዎች ጸጥ ብለው በምድር ላይ ተቀመጡ፤ እነርሱ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ማቅ ለበሱ፤ የኢየሩሳሌም ልጃገረዶች አንገታቸውን ደፉ። ሕዝቤ ስለ ተፈጀ፥ ሕፃናት በከተማይቱ መንገዶች ላይ ስለሚዝለፈለፉ፥ ዐይኖቼ በለቅሶ ደከሙ፤ አንጀቴ ተንሰፈሰፈ፤ ተስፋም ቈረጥሁ። በጦር ሜዳ እንደ ቈሰለ ወታደር በከተማው መንገዶች እየተዝለፈለፉ በእናታቸው ክንድ ላይ ሆነው፥ “ምግብና ውሃ!” እያሉ እያለቀሱ፥ ሕይወታቸው ያልፋል። ምን ልበላችሁ? ከምንስ ጋር ላነጻጽራችሁ? የተወደደችው ከተማ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! እንዳጽናናችሁ ከምን ጋር ላመሳስላችሁ? በተለይ የኢየሩሳሌም ከተማ ሕዝብ ሆይ! የሚደርስባችሁ ጥፋት እንደ ባሕር መጠኑ ሰፊ ስለ ሆነ፥ ማን ሊፈውሳችሁ ይችላል? የእናንተ ነቢያት ሐሰተኛና አታላይ ራእይ አይተውላችኋል፤ ሐሰተኛና አሳሳች ትንቢት ተናገሩ እንጂ፥ ዕድል ፈንታችሁን ለመለወጥ በደላችሁን አላጋለጡም። “ፍጹም ውብ ናት የሚሏት የዓለም መደሰቻ የነበረችው ከተማ ይህች ናትን?” እያሉ በመንገድ የሚያልፉ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ እጃቸውን እያጨበጨቡ ራሳቸውን በመነቅነቅ አሽሟጠጡ። ጠላቶቻችሁ ሁሉ በእናንተ ላይ አፋቸውን ይከፍታሉ፤ ያሽሟጥጣሉ ጥርሳቸውን ያፋጫሉ፤ እንዲህ ሲሉም ይጮኻሉ፦ “ደመሰስናቸው! እሰይ ይህ የምንመኘው ቀን ነበር! በመጨረሻም አየነው።” እግዚአብሔር ያሰበውን ፈጸመ፤ ቀድሞ የተናገረውን ቃል ተግባራዊ አደረገ፤ ከረጅም ጊዜ በፊት በወሰነው መሠረት ያለ ርኅራኄ አፈራረሰ፤ ጠላት በእናንተ ላይ ደስ እንዲሰኝ አደረገ፤ የጠላቶቻችሁንም ኀይል አበረታ። በኢየሩሳሌም ቅጥር ውስጥ የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር ጩኹ! ዕንባችሁም ሌሊትና ቀን እንደ ጐርፍ ይውረድ፤ በፍጹም ዕረፍት አታድርጉ፤ ለዐይኖቻችሁም ፋታን አትስጡ። እናንተ ሌሊቱን በሙሉ ተነሥታችሁ ጩኹ፤ በልባችሁ የሚሰማችሁን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ፊት አቅርቡ፤ በየመንገዱ ማእዘን በራብ ለሚዝለፈለፉ ልጆቻችሁ ሕይወት በጸሎት እጆቻችሁን ወደ እግዚአብሔር አንሡ።