ከዮርዳኖስ ማዶ በተራራማውና በቈላማው አገሮች፥ በሜዲቴራኒያን ባሕር ጠረፍ፥ እስከ ሊባኖስ ድረስ ያሉት የሒታውያን፥ የአሞራውያን፥ የከነዓናውያን፥ የፔሩዛውያን የኤዊያውያንና የኢያቡሳውያን ነገሥታት ይህን በሰሙ ጊዜ፥ ኀይላቸውን በአንድነት አስተባብረው በኢያሱና በእስራኤላውያን ላይ ለመዝመት መጡ። የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በዐይ ከተማዎች ላይ ያደረገውን ሁሉ ስለ ሰሙ፤ እርሱን ለማታለል ወሰኑ፤ እነርሱም ስንቃቸውን አዘጋጅተው፥ አሮጌ ስልቻና ቀዳዳው ተለጥፎ የተሰፋ የወይን ጠጅ አቁማዳ በአህዮች ጫኑ፤ ተቀዳዶ ያለቀ አሮጌ ልብስ ለብሰው፥ የተጠጋገነ እላቂ ጫማ አደረጉ፤ ለስንቅ የያዙትም እንጀራ ደረቅና የሻገተ ነበር። ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በጌልገላ ወደሚገኘው ሰፈር ሄደው ኢያሱንና እስራኤላውያንን፦ “እኛ የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ የመጣነውም ከእናንተ ጋር የቃል ኪዳን ውል ለማድረግ ነው” አሉአቸው። የእስራኤል ሰዎች ግን የገባዖንን ሰዎች “ከእናንተ ጋር እንዴት ውል እናደርጋለን? ምናልባትም እናንተ በእኛ መካከል የምትኖሩ ልትሆኑ ትችላላችሁ” አሉአቸው። የገባዖንም ሰዎች ኢያሱን “እኛ አገልጋዮችህ ነን” አሉት። ኢያሱም “እናንተ እነማን ናችሁ? የመጣችሁትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ይህን ታሪክ ነገሩት፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር በግብጽ ያደረገውን ሁሉ ስለ ሰማን እኛ የመጣነው በጣም ሩቅ ከሆነ አገር ነው፤ እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ በስተምሥራቅ በነበሩት በሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት ላይ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል፤ እነዚህም ሁለቱ ነገሥታት በዐስታሮት ይኖሩ የነበሩት የሐሴቦን ንጉሥ ሲሖንና የባሳን ንጉሥ ዖግ ናቸው። መሪዎቻችንና በምድራችን የሚኖሩት ሕዝቦች ሁሉ ለመንገዳችን የሚሆነንን ስንቅ አዘጋጅተን መጥተን ከእናንተ ጋር እንድንገናኝ ልከውናል፤ ለእናንተ የምንታዘዝ አገልጋዮች እንድንሆንና እናንተም ከእኛ ጋር የሰላም ውል እንድታደርጉ እንጠይቃችሁ ዘንድ አዘውናል። የያዝነውን ስንቅ ተመልከቱ! ከቤት ተነሥተን ከእናንተ ጋር ለመገናኘት ጒዞ ስንጀምር ገና ትኩስ እንጀራ ነበር፤ አሁን ግን ደረቅና የሻገተ መሆኑን ተመልከቱ! እነዚህንም የወይን አቁማዳዎች በሞላናቸው ጊዜ ገና አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን የተቀደዱ መሆናቸውን ተመልከቱ! ከጒዞው ርቀት የተነሣ እነሆ፥ ልብሳችንም ጫማችንም አልቆአል።” የእስራኤልም ሰዎች ከመንገደኞቹ ስንቅ ጥቂት ወሰዱ፤ ስለ ሁኔታው ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ አልጠየቁም። ስለዚህም ኢያሱ ከእነርሱ ጋር ለሕይወታቸው ዋስትና ቃል ኪዳን በመግባት የሰላም ስምምነት አደረገ። የእስራኤል ሕዝብ መሪዎችም ስምምነቱን ለመጠበቅ ቃል ገቡላቸው።
መጽሐፈ ኢያሱ 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 9:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች