መጽሐፈ ኢያሱ 6:20-27
መጽሐፈ ኢያሱ 6:20-27 አማ05
ስለዚህ እምቢልታ ተነፋ፤ ሕዝቡም የእምቢልታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ አሰሙ የከተማይቱም ቅጽሮች ፈረሱ፤ ከዚህም በኋላ ሠራዊቱ ኮረብታውን ወጥቶ ሰተት ብሎ ወደ ከተማይቱ በመግባት በቊጥጥሩ ሥር አደረጋት፤ ሰይፋቸውንም መዘው በከተማይቱ የተገኘውን ወንዱንም ሴቱንም ወጣቱንና ሽማግሌውን ሁሉ ገደሉ፤ የከብት፥ የበግና የአህያውን መንጋ ሁሉ ፈጁ። ኢያሱ ሰላዮች ሆነው የተላኩትን ሁለት ሰዎች “ወደ ጋለሞታይቱ ረዓብ ቤት ሄዳችሁ በገባችሁላት የተስፋ ቃል መሠረት እርስዋንና ቤተሰብዋን አውጡ” አላቸው። እነርሱም ሄደው ረዓብን ከአባትዋና ከእናትዋ ከወንድሞችዋና ከሌሎችም የእርስዋ ወገን ከሆኑት ሰዎች ሁሉ ጋር አውጥተው ከእስራኤላውያን ሰፈር ውጪ አኖሩአቸው። ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ዕቃ ግምጃ ቤት ካስቀመጡአቸው ከብሩና ከወርቁ እንዲሁም በነሐስና በብረት ከተሠሩት ዕቃዎች በቀር ከተማይቱንና በእርስዋ ያሉትን ነገሮች ሁሉ አቃጠሉ። ነገር ግን ጋለሞታይቱ ረዓብ ኢያሱ ወደ ኢያሪኮ የላካቸውን ሁለቱን ሰላዮች ደብቃ ከሞት ስላዳነች እርሱ እርስዋን፥ ቤተ ዘመዶችዋንና ከእርስዋ ጋር ያሉትን ሌሎች ሰዎች ሁሉ ከሞት አተረፈ፤ የእርስዋም ዘሮች እስከ አሁን ድረስ በእስራኤል ምድር ይኖራሉ። በዚያን ጊዜ ኢያሱ፦ “ይህቺን የኢያሪኮን ከተማ ለመገንባት የሚነሣ የተረገመ ይሁን፤ መሠረቱን ሲጥል የበኲር ልጁ ይጥፋ፤ መዝጊያውን ሲያቆም የመጨረሻ ልጁ ይጥፋ፤” ብሎ ረገመ። በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የኢያሱ ዝና በአገሪቱ ሁሉ ተሰማ።

