“ኢዮብ ሆይ! መልስ የሚሰጥህ ሰው ብታገኝ እስቲ ተጣራ፤ ርዳታ ይሰጥህ ዘንድ ከመላእክቱ ወደ ማንኛው ትመለከታለህ? ቊጣ ሞኝን ይገድለዋል፤ ቅናትም ሰውን ያጠፋል። ሞኝ ደርጅቶ ሲኖር አየሁ፤ በእግዚአብሔር ቊጣ በድንገት መኖሪያው ፈራረሰ። ልጆቹም የኑሮ ዋስትና አያገኙም፤ በአደባባይም የሚከራከርላቸው ስለማያገኙ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ሰብሉንም የተራቡ ሰዎች ይበሉታል፤ በእሾኽ መካከል የበቀለውን እንኳ አይተውለትም፤ የተጠሙ ሰዎችም ሀብቱን ለመውሰድ ይጐመዣሉ። ችግር ከዐፈር አይነሣም፤ መከራም ከመሬት አይበቅልም። የእሳት ፍንጣሪ ከፍም ላይ ተነሥቶ ወደ ዐየር እንደሚበር፥ እንደዚሁም ሰው ለመከራ ይወለዳል። “እኔ አንተን ብሆን ኖሮ ወደ እግዚአብሔር እማጠን ነበር፤ ችግሬን ሁሉ እገልጥለት ነበር። እርሱ የማይቈጠረውን ተአምራት፦ የማይመረመረውን ታላቅ ነገር ያደርጋል። በምድር ላይ ዝናብን ያዘንባል፤ እርሻዎችንም በውሃ ያረሰርሳል። የተዋረዱትን በክብር ከፍ ያደርጋቸዋል፤ ያዘኑትንም በማጽናናት ደስ ያሰኛቸዋል። ሥራቸው እንዳይሳካ የተንኰለኞችን ዕቅድ ከንቱ ያደርጋል። ጥበበኞችን የራሳቸው ተንኰል ወጥመድ ሆኖ እንዲይዛቸው ያደርጋል የተንኰለኞችም ዕቅድ በፍጥነት ይጠፋል። ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል፤ ገና በእኩለ ቀን፥ በሌሊት ጨለማ ውስጥ እንዳሉ ሆነው ይደናበሩ። ድኾችን ከጠላቶቻቸው ሰይፍ ያድናቸዋል፤ ችግረኞችንም ከጨቋኞች እጅ ነጻ ያወጣቸዋል። ለድኾች ተስፋ ይሰጣል፤ ዐመፅንም ከምድረ ገጽ ያጠፋል። “እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው የተባረከ ነው! ስለዚህ የልዑል እግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ። እግዚአብሔር ቢያቈስልህም መልሶ ይጠግንሃል፤ በአንድ እጁ ቢጐዳህ በሌላ እጁ ይፈውስሃል። ከስድስት ዐይነት የመቅሠፍት አደጋዎች ይታደግሃል፤ በሰባተኛውም ምንም ጒዳት አይደርስብህም። በራብ ዘመን በሕይወት ያኖርሃል። በጦርነትም ጊዜ ከሞት ያድንሃል። እግዚአብሔር ከክፉ ምላስ ይጠብቅሃል፤ ጥፋት ቢመጣብህም አትፈራም። የኀያላን አጥቂነትና ራብ አያስደነግጡህም፤ የምድርንም አራዊት አትፈራም። በምታርሰው መሬት ላይ ድንጋይ አያውክህም፤ ከአራዊትም ጋር በሰላም ትኖራለህ። በድንኳንህ ሰላም እንደሚሰፍን ታረጋግጣለህ፤ የበጎችህንም በረት ስትጐበኝ ሁሉን በደኅና ታገኛቸዋለህ። ትውልድህ እንደሚበዛ ታውቃለህ፤ ዘርህም እንደ መስክ ሣር ይበዛል። የስንዴ እሸት እስኪጐመራ በማሳ ላይ እንደሚቈይ አንተም በዕድሜ እስከምትሸመግል ትኖራለህ። እኛ ይህን ሁሉ መርምረን እውነት መሆኑን ዐውቀናል አንተም አስተውለህ ተግባራዊ አድርገው።”
መጽሐፈ ኢዮብ 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 5:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች