ከዕለታት አንድ ቀን የኢዮብ ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ ይደሰቱ ነበር። በዚያኑ ዕለት አንድ መልእክተኛ ወደ ኢዮብ መጥቶ እንዲህ አለ፦ “በሬዎች ጠምደን እናርስ ነበር፤ አህዮችም በአጠገባችን ባለው መስክ ተሰማርተው ነበር፤ የሳባ ሰዎች መጥተው አደጋ በመጣል ሁሉንም ዘርፈው ወሰዱ፤ አገልጋዮችህን ሁሉ በሰይፍ ገደሉአቸው፤ እኔ ብቻ አምልጬ የሆነውን ነገር ልነግርህ መጣሁ።” የመጀመሪያው መልእክተኛ ንግግሩን ገና ሳይጨርስ ሌላ መልእክተኛ መጣና “በጎቹንና እረኞቹን በሙሉ መብረቅ ከሰማይ ወርዶ ገደላቸው፤ እኔ ብቻ አምልጬ የሆነውን ነገር ልነግርህ መጣሁ” አለው። ይኸኛው መልእክተኛ ተናግሮ ሳይጨርስ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፥ “በሦስት ቡድን የተከፈሉ የከለዳውያን ዘራፊዎች በድንገት አደጋ ጣሉብን፤ ግመሎቹን በሙሉ ወሰዱአቸው፤ አገልጋዮችህንም በሙሉ በሰይፍ ገደሉአቸው፤ እኔ ብቻ አምልጬ የሆነውን ነገር ልነግርህ መጣሁ” አለው። ይኸኛው መልእክተኛም ተናግሮ ሳይጨርስ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ “ልጆችህ በሙሉ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ ይደሰቱ ነበር፤ ከበረሓ የተነሣ ዐውሎ ነፋስ በድንገት መጥቶ ቤቱን በሙሉ በገለባበጠው ጊዜ ቤቱ በላያቸው ላይ ስለ ተደረመሰ ሞቱ፤ እኔ ብቻ አምልጬ የሆነውን ነገር ልነግርህ መጣሁ” አለው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮብ ተነሥቶ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ራሱን ተላጨ፤ በግምባሩም ወደ መሬት ተደፍቶ በመስገድ፥ “ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ተወለድኩ፤ ስሞትም ራቁቴን እሄዳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ወሰደ፤ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን!” አለ።
መጽሐፈ ኢዮብ 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 1:13-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች