የዮሐንስ ወንጌል 9:18-41

የዮሐንስ ወንጌል 9:18-41 አማ05

ይህ ሰው ዕውር እንደ ነበረና ዐይኖቹም በኋላ እንዴት እንደ ተከፈቱ ወላጆቹን ጠርተው እስከ ጠየቁአቸው ድረስ የአይሁድ ባለ ሥልጣኖች አላመኑም ነበር። ስለዚህ ወላጆቹን፥ “ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? አሁንስ እንዴት ማየት ቻለ?” ሲሉ ጠየቁአቸው። ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይህ ሰው ልጃችን መሆኑንና ዕውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ ነገር ግን አሁን እንዴት እንደሚያይና ዐይኖቹንም ማን እንደአበራለት አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ እርሱ በዕድሜው ሙሉ ሰው ስለ ሆነ ስለ ራሱ መናገር ይችላል።” ወላጆቹ ይህን ያሉት ኢየሱስን “መሲሕ ነው” የሚል ሰው ቢኖር የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከምኲራብ ሊያስወጡት ተስማምተው ስለ ነበረ እነርሱን በመፍራት ነበር። ስለዚህ ወላጆቹ፥ “እርሱ በዕድሜው ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱን ጠይቁት” አሉ። በዚህ ምክንያት ዕውር የነበረውን ሰው እንደገና ጠርተው “አንተ እውነቱን በመናገር እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። ዕውር የነበረውም ሰው፥ “እርሱ ኃጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ አንድ ነገር ዐውቃለሁ፤ ይኸውም እኔ ዕውር እንደ ነበርኩና አሁን ማየት እንደ ቻልኩ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። እነርሱም “ምን አደረገልህ? ዐይኖችህንስ ያዳነው እንዴት ነው?” አሉት። እርሱም “አስቀድሜ ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን መስማት አልፈለጋችሁም፤ ታዲያ፥ ስለምን እንደገና መስማት ትፈልጋላችሁ? እናንተም የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆን ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ እያሉ ሰደቡት፦ “የእርሱስ ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ ሆነ አናውቅም።” ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ይህ ሰው ከየት እንደ ሆነ አለማወቃችሁ ያስደንቃል! ነገር ግን ዐይኖቼን የአበራ እርሱ ነው። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንደማይሰማ የታወቀ ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚያመልክና ፈቃዱንም የሚፈጽም ሰው ሲኖር እርሱን እግዚአብሔር ይሰማዋል። ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዐይኖች ያበራ አለ ሲባል ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ለማድረግ ባልቻለም ነበር።” እነርሱም “ሁለንተናህ በኃጢአት ተወርሶ የተወለድክ! አንተ እኛን ልታስተምር ነውን?” አሉና ከምኲራብ አስወጡት። ሰውየውን ከምኲራብ እንዳስወጡት ኢየሱስ ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! በእርሱ እንዳምን እርሱ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስ “ከዚህ በፊት አይተኸዋል፤ አሁንም የሚያነጋግርህ እርሱ ነው” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! አምናለሁ” ብሎ ሰገደለት። ኢየሱስም “የማያዩ እንዲያዩ፥ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቼአለሁ” አለ። በዚያን ጊዜ በኢየሱስ አጠገብ የነበሩ ፈሪሳውያን ይህን ሰምተው “ታዲያ፥ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነውን?” አሉት። ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፥ ኃጢአተኞች ሆናችሁ ትቀራላችሁ” አላቸው።