ትንቢተ ኢሳይያስ 58:3-7
ትንቢተ ኢሳይያስ 58:3-7 አማ05
ሕዝቡም “እነሆ እኛ እንጾማለን፤ አንተ ግን አትመለከተንም፤ የማትመለከተንስ ከሆነ ሰውነታችንን ለምን እናዋርዳለን?” ይላሉ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “እነሆ እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ የልባችሁን ፈቃድ ትፈጽማላችሁ፤ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ትጨቊናላችሁ፤ የጾማችሁ መጨረሻው ጠብና ጭቅጭቅ ስለ ሆነ ጭካኔ በተሞላበት ቡጢ ትማታላችሁ፤ እንደዚህ አድርጋችሁ የምትጾሙት ጾም ጸሎታችሁን በላይ በሰማይ እንዲሰማ አያደርገውም። እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ ሰውነታችሁን ታጐሳቊላላችሁ፤ ራሳችሁን እንደ ሸምበቆ ዝቅ ታደርጋላችሁ፤ አመድ ነስንሳችሁ፥ ማቅም አንጥፋችሁ ትተኛላችሁ? ታዲያ እናንተ ጾም የምትሉት ይህን ነውን? እኔስ በዚህ ዐይነቱ ጾም ደስ የሚለኝ ይመስላችኋልን? “እኔ የምደሰትበት ጾም የጭቈና ሰንሰለትና የፍትሕ መጓደል ቀንበር ታላሉ ዘንድ፥ ቀንበሩን ሰብራችሁ የተጨቈኑትን ነጻ ታወጡ ዘንድ አይደለምን? ምግባችሁን ከተራበ ሰው ጋር እንድትካፈሉ፥ ማደሪያ የሌለውን ድኻ በቤታችሁ እንድትቀበሉ፥ የተራቈቱትን እንድታለብሱ፥ ከቅርብ ዘመዶቻችሁም ራሳችሁን እንዳትደብቁ አይደለምን?

