ኦሪት ዘፍጥረት 18:22-33

ኦሪት ዘፍጥረት 18:22-33 አማ05

ከዚህ በኋላ ሁለቱ ሰዎች ወደ ሰዶም ለመሄድ ተነሡ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ቈየ፤ ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ በደል የሌለባቸውን ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህን? በከተማይቱ ውስጥ ኀምሳ ደጋግ ሰዎች ቢገኙ ከተማይቱን በሙሉ ትደመስሳለህን? ስለ ኀምሳው ደጋግ ሰዎች ስትል ከተማይቱ እንዳትጠፋ አታደርግምን? በደል ያልሠሩትን ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህ ብዬ አላስብም፤ ይህንን እንደማታደርገው አምናለሁ፤ ይህንንማ ካደረግህ ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር መቀጣታቸው ነው፤ ይህ ከቶ አይሆንም! የዓለም ሁሉ ፈራጅ በትክክል መፍረድ ይገባው የለምን?” እግዚአብሔርም “በሰዶም ከተማ ውስጥ በደል ያልሠሩ ኀምሳ ደጋግ ሰዎች ባገኝ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን ፈጽሞ አላጠፋም” አለ። አብርሃም እንደገና እንዲህ አለ፤ “እኔ ትቢያና ዐመድ የሆንኩ ከንቱ ሰው፥ ከጌታዬ ጋር በድፍረት በመነጋገሬ ይቅር በለኝ፤ ነገር ግን የደጋግ ሰዎች ቊጥር ኀምሳ መሆኑ ቀርቶ አርባ አምስት ቢሆን፥ አምስት ስለ ጐደለ ከተማይቱን በሙሉ ታጠፋለህን?” እግዚአብሔርም “አርባ አምስት ደጋግ ሰዎች ባገኝ ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። አብርሃምም “አርባ ብቻ እዚያ ቢገኙስ?” ብሎ እንደገና ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አርባ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ እባክህ አትቈጣ፤ እንደገና ልናገር፤ ምናልባት ሠላሳ ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እግዚአብሔርም “ሠላሳ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ አሁንም እንደገና በመናገሬ ይቅር በለኝ፤ ምናልባት ኻያ ቢገኙስ?” አለ፤ እግዚአብሔርም “ኻያ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ እባክህ አትቈጣ አንድ ጊዜ ልናገር፤ ዐሥር ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እግዚአብሔርም “ዐሥር ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ተነጋግሮ ካበቃ በኋላ ከዚያ ስፍራ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}