ኦሪት ዘፍጥረት 14:12-24

ኦሪት ዘፍጥረት 14:12-24 አማ05

የአብራም የወንድም ልጅ ሎጥ በሰዶም ይኖር ስለ ነበር እርሱን ማርከው፥ ሀብቱንም ሁሉ ይዘው ሄዱ። ነገር ግን አንድ ሰው ሸሽቶ መጣና የሆነውን ሁሉ ለዕብራዊው ለአብራም ነገረው፤ በዚያን ጊዜ አብራም የሚኖረው በአሞራዊው መምሬ የተቀደሱ የወርካ ዛፎች አጠገብ ነበር፤ መምሬና ወንድሞቹ ኤሽኮል፥ ዐኔር የአብራም የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞች ነበሩ። አብራም የወንድሙ ልጅ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ ተወልደው የጦር ልምምድ ያላቸውን 318 ሰዎች በትጥቅ አደራጅቶ አራቱን ነገሥታት በመከታተል እስከ ዳን ድረስ ሄደ። እዚያ ሰዎቹን በቡድን ከፋፍሎ እርሱና አገልጋዮቹ ከጠላቶቹ ጋር በሌሊት ጦርነት ገጥመው ድል አደረጋቸው፤ ከደማስቆ በስተሰሜን እስከሚገኘው እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። የተወሰደውንም ምርኮ ሁሉ መልሶ አመጣ፤ እንዲሁም የወንድሙን ልጅ ሎጥን ከነሀብቱ መልሶ አመጣ፤ ከእነርሱም ጋር ሴቶችና ሌሎች እስረኞች ነበሩ። አብራም ከዶርላዖሜርና ከእነርሱ ጋር አብረው የነበሩትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፥ የሰዶም ንጉሥ “የንጉሥ ሸለቆ” እየተባለ በሚጠራው በሻዌህ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ፤ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅም ለአብራም እንጀራና የወይን ጠጅ አመጣለት፤ እንዲህ ብሎም አብራምን ባረከው፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል እግዚአብሔር አብራምን ይባርክ! በጠላቶችህ ላይ ድልን ያቀዳጀህ፥ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።” አብራምም በምርኮ ካገኘው ሀብት ሁሉ አንድ ዐሥረኛውን ለመልከ ጼዴቅ ሰጠው። የሰዶምም ንጉሥ አብራምን “በምርኮ ያገኘኸውን ሀብት ሁሉ ለራስህ ውሰድ፤ ሰዎቼን ግን መልስልኝ” አለው። አብራምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በልዑል እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ አንተ ‘አብራምን ሀብታም ያደረግኹት እኔ ነኝ’ እንዳትል ሌላው ቀርቶ አንዲት ክር ወይም የጫማ ማሰሪያ እንኳ ከአንተ አልወስድም። ስለዚህ ለራሴ ምንም ነገር አልወስድም፤ የእኔ ሰዎች የያዙትን እንዲወስዱ እስማማለሁ፤ እንዲሁም የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞቼ ዐኔር፥ ኤሽኮልና መምሬ ድርሻቸውን ይውሰዱ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}