ወደ ገላትያ ሰዎች 4:1-6

ወደ ገላትያ ሰዎች 4:1-6 አማ05

አሁንም የምለው ይህን ነው፤ ወራሹ ሕፃን ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ምንም እንኳ የንብረቱ ሁሉ ጌታ ቢሆን ከባሪያ በምንም አይለይም። ነገር ግን አባቱ የወሰነለት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በሞግዚቶችና በመጋቢዎች ሥር ነው። እንዲሁም እኛ በመንፈሳዊ ነገር እንደ ሕፃናት በነበርንበት ጊዜ ለዚህ ዓለም ሥርዓት ተገዢዎች ሆነን ባሪያዎች ነበርን። ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን፤ እርሱ ከሴት ተወለደ፤ ለሕግም ታዛዥ ሆነ። ይህንንም ያደረገው ከሕግ ሥር ያሉትን ለመዋጀትና እኛም የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ለማድረግ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችንም እግዚአብሔርን “አባባ” እያለ የሚጠራውን የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።