ገላትያ 4:1-6
ገላትያ 4:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን እላለሁ፤ ወራሹ ሕፃን ሳለ ለሁሉ ጌታ ሲሆን ከአገልጋይ የሚለይ አይደለም። ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ዕድሜ ድረስ በአያት ወይም በሞግዚት እጅ ይጠበቃል። እንዲሁ እኛም ሕፃናት በነበርን ጊዜ፥ ለዚህ ዓለም ስሕተት ተገዝተን ነበር። ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፤ ከሴትም ተወለደ፤ የኦሪትንም ሕግ ፈጸመ። እኛ የልጅነትን ክብር እንድናገኝ በኦሪት የነበሩትን ይዋጅ ዘንድ። ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር አባ አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ።
ገላትያ 4:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኔ የምለው ይህ ነው፤ ወራሹ ሕፃን እስከ ሆነ ድረስ፣ ሀብት ሁሉ የርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ከባሪያ የተለየ አይደለም። አባቱ እስከ ወሰነለት ጊዜ ድረስ በጠባቂዎችና በሞግዚቶች ሥር ነው። እኛም እንዲሁ ገና ልጆች በነበርንበት ጊዜ፣ ከዓለም መሠረታዊ መንፈሳዊ ኀይሎች ሥር በመሆን በባርነት ተገዝተን ነበር። ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “ አባ ፣ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።
ገላትያ 4:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥ ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤ ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።
ገላትያ 4:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አሁንም የምለው ይህን ነው፤ ወራሹ ሕፃን ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ምንም እንኳ የንብረቱ ሁሉ ጌታ ቢሆን ከባሪያ በምንም አይለይም። ነገር ግን አባቱ የወሰነለት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በሞግዚቶችና በመጋቢዎች ሥር ነው። እንዲሁም እኛ በመንፈሳዊ ነገር እንደ ሕፃናት በነበርንበት ጊዜ ለዚህ ዓለም ሥርዓት ተገዢዎች ሆነን ባሪያዎች ነበርን። ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን፤ እርሱ ከሴት ተወለደ፤ ለሕግም ታዛዥ ሆነ። ይህንንም ያደረገው ከሕግ ሥር ያሉትን ለመዋጀትና እኛም የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ለማድረግ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችንም እግዚአብሔርን “አባባ” እያለ የሚጠራውን የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።
ገላትያ 4:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህንን እላለሁ፤ ወራሹ በሕፃንነት ዘመኑ ሁሉ፥ ምንም እንኳ የሁሉ ጌታ ቢሆንም ከባርያ አይለይም፤ ነገር ግን አባቱ እስከወሰነለት ጊዜ ድረስ በጠባቂዎችና በመጋቢዎች ሥር ነው። እኛም ደግሞ ሕፃናት በነበርንበት ጊዜ ከዓለም የመጀመሪያ ትምህርቶች ሥር ተገዝተን ነበር፤ የዘመኑ ሙላት በመጣ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግ ሥር የተወለደውን ልጁን ላከ፤ ይህም ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት፥ እኛም ልጅነትን እንድናገኝ ነው። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር “አባ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።