የሐዋርያት ሥራ 8:1-9
የሐዋርያት ሥራ 8:1-9 አማ05
ሳውልም በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ ነበር፤ እስጢፋኖስ በሞተበት ቀን በኢየሩሳሌም በምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ተነሣ፤ ከሐዋርያት በቀር አማኞች ሁሉ ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ ምድር ተበተኑ። አንዳንድ መንፈሳውያን ሰዎች እስጢፋኖስን ቀበሩት፤ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ አለቀሱለት። ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ይጥር ነበር፤ ከቤት ወደ ቤትም እየገባ ወንዶችና ሴቶች አማኞችን እየጐተተ ያወጣ ነበር፤ ወደ እስር ቤትም ያስገባቸው ነበር። የተበተኑትም አማኞች በሄዱበት ስፍራ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምሩ ነበር። ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ሄዶ ሰዎቹን ስለ መሲሕ አስተማራቸው። ሰዎቹም የፊልጶስን ቃል በሰሙና የሚያደርጋቸውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በአንድ ሐሳብ በጥንቃቄ ያዳምጡት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበር፤ ብዙ ሽባዎችና አንካሶችም ይድኑ ነበር። ስለዚህ በዚያች ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። በዚያች ከተማ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው በከተማይቱ ውስጥ አስማት እያደረገ የሰማርያን ሕዝብ ሲያስደንቅ ቈይቶአል፤ “እኔ ትልቅ ሰው ነኝ!” እያለም ይናገር ነበር።

