የሐዋርያት ሥራ 13:24-52

የሐዋርያት ሥራ 13:24-52 አማ05

ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ የንስሓን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስ ሥራውን በጨረሰ ጊዜ ‘እኔ ማን መሰልኳችሁ? እኔ መሲሕ አይደለሁም፤ ነገር ግን የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ከእኔ በኋላ ሌላ ይመጣል’ ይል ነበር። “እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞችና እናንተም እግዚአብሔርን የምትፈሩ አሕዛብ! ይህ የመዳን ቃል የተላከው ለእኛ ነው። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን አላወቁም፤ በየሰንበቱም የሚነበቡትን የነቢያት መጻሕፍት ባለማስተዋላቸው በእርሱ ላይ በፈረዱበት ጊዜ ትንቢቱ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርገዋል። ምንም እንኳ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት ባያገኙበት እርሱን እንዲገድልላቸው ጲላጦስን ለመኑት። ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙበት በኋላ ከመስቀል አውርደው ቀበሩት፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው። ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር ለመጡትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን በሕዝብ ፊት ምስክሮቹ ናቸው። እኛም ይዘንላችሁ የመጣነው እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በተስፋ የሰጠውን መልካም ዜና ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት በማስነሣቱ ይህንኑ ተስፋ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞታል፤ ይህም በሁለተኛው መዝሙር፥ ‘አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። መበስበስ እንዳይደርስበት እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣው ለማስረዳት፥ ‘ቅዱሱን የታመነ በረከትን ለዳዊት የተሰጠውን ተስፋ እሰጣችኋለሁ’ ብሎ ተናግሮአል። ደግሞም በሌላ መዝሙር፥ ‘ቅዱሱ ልጅህ መበስበስ እንዲደርስበት አታደርገውም’ ይላል። ነገር ግን ዳዊት በሕይወቱ ዘመን አገልግሎቱን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከፈጸመ በኋላ ሞቶአል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮአል፤ መበስበስም ደርሶበታል። እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣው ግን መበስበስ አልደረሰበትም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ ነጻ ሊያወጣው ከማይችለው ኃጢአት ሁሉ ነጻ ይወጣል። ስለዚህ በነቢያት እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ‘እናንተ ፌዘኞች እዩ! ተደነቁ! ጥፉም! ማንም ሰው ቢያወራላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁ።’ ” ጳውሎስና በርናባስ ከምኲራብ ሲወጡ ይህንኑ ነገር በሚመጣው ሰንበት እንደገና እንዲነግሩአቸው ሰዎቹ ለመኑአቸው። የምኲራቡ ጉባኤ በተበተነ ጊዜ ብዙ የአይሁድ ወገኖችና ወደ አይሁድ እምነት ገብተው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሰዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ ጳውሎስና በርናባስም ሰዎቹን በማስተማር በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አሳሰቡአቸው። በሚቀጥለው ሰንበት ከከተማው ነዋሪዎች አብዛኞቻቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ፤ አይሁድ የሕዝቡን ብዛት ባዩ ጊዜ በቅናት ተሞሉ፤ ንግግሩንም እየተቃወሙ ጳውሎስን ሰደቡት፤ ጳውሎስና በርናባስ ግን እንዲህ ሲሉ በድፍረት ተናገሩ፤ “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ እንዲነገር አስፈላጊ ነው፤ እናንተ አንቀበልም ካላችሁና የዘለዓለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን እነሆ፥ እኛ ዞር ብለን ወደ አሕዛብ እንሄዳለን። ይህንንም የምናደርገው ጌታ፦ ‘መዳንን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንድታመጣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ’ በማለት ስላዘዘን ነው።” አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ የጌታንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወት የተመረጡትም ሁሉ አመኑ። የጌታም ቃል በዚያ አገር ሁሉ ተስፋፋ። የአይሁድ መሪዎች ግን የአይሁድ እምነት ተከታዮች የሆኑትን ሀብታሞች ሴቶችና የከተማውን ታላላቅ ሰዎች አሳድመው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት እንዲነሣ አደረጉ፤ ከአገራቸውም አስወጡአቸው። ጳውሎስና በርናባስም በእነርሱ ላይ የእግራቸውን አቧራ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።