ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት፣ ዮሐንስ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ንስሓ ገብተው እንዲጠመቁ ሰብኮላቸው ነበር። ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ፣ ‘እኔ ማን መሰልኋችሁ? እኔ እኮ እርሱ አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግሩን ጫማ መፍታት የማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር። “እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞች፤ ደግሞም በመካከላችሁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፤ ይህ የድነት መልእክት የተላከው ለሁላችንም ነው። የኢየሩሳሌም ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስን አላወቁትም፤ ይሁን እንጂ በየሰንበቱ የሚነበበው የነቢያት ቃል እንዲፈጸም በርሱ ፈረዱበት። ለሞት የሚያበቃው አንድም ምክንያት ባያገኙበትም እንኳ ጲላጦስ የሞት ፍርድ እንዲፈርድበት ተማጸኑት። ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከተሰቀለበት ዕንጨት አውርደው በመቃብር ውስጥ አስገቡት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው። ከገሊላ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋራ ለነበሩትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን ለሕዝቡ ምስክሮቹ ናቸው። “እኛም እግዚአብሔር ለአባቶች ቃል የገባውን የምሥራች ቃል ለእናንተ እንሰብካለን፤ ኢየሱስንም ከሙታን በማስነሣቱ ለእነርሱ የገባውን ቃል ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሟል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር እንዲህ ብሎ ተጽፏል፤ “ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።’ ደግሞም፣ እርሱ እንዳልበሰበሰና እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ለማረጋገጥ እንዲህ ብሏል፤ “ ‘የተቀደሰውንና የታመነውን፣ የዳዊትን በረከት እሰጣችኋለሁ።’ ስለዚህ በሌላም ስፍራ፣ “ ‘ቅዱስህ መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም’ ይላል። “ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካገለገለ በኋላ አንቀላፍቷል፤ ከአባቶቹም ጋራ ተቀብሮ ሥጋው በስብሷል። እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሣው እርሱ ግን መበስበስን አላየም። “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ “ ‘እናንተ ፌዘኞች፤ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ ማንም ቢነግራችሁ እንኳን፣ የማታምኑትን ነገር፣ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ” ጳውሎስና በርናባስ ከምኵራብ ሲወጡ፣ ሰዎቹ ስለዚሁ ነገር በሚቀጥለው ሰንበት እንዲነግሯቸው ለመኗቸው። ጉባኤው ከተበተነ በኋላም፣ ብዙ አይሁድና ወደ ይሁዲ ሃይማኖት ገብተው በመንፈሳዊ ነገር የበረቱ ሰዎች፣ ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው፤ እነርሱም አነጋገሯቸው፤ በእግዚአብሔርም ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ መከሯቸው። በሚቀጥለውም ሰንበት የከተማው ሕዝብ፣ ጥቂቱ ሰው ብቻ ሲቀር፣ በሙሉ የጌታን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ። አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ፣ በቅናት ተሞሉ፤ የጳውሎስንም ንግግር እየተቃወሙ ይሰድቡት ነበር። ጳውሎስና በርናባስም በድፍረት እንዲህ አሏቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገር አለበት፤ እናንተ ግን ናቃችሁት፤ በዚህም የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ ስለ ፈረዳችሁ፣ እኛም ወደ አሕዛብ ዞር ለማለት እንገደዳለን። ደግሞም ጌታ እንዲህ ብሎ አዝዞናል፤ “ ‘ድነትን እስከ ምድር ዳርቻ ታደርስ ዘንድ፣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ።’ ” አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ለጌታም ቃል ክብርን ሰጡ፤ ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትም ሁሉ አመኑ። የጌታም ቃል በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ተስፋፋ። አይሁድ ግን በመንፈሳዊ ነገር የተጉትንና የከበሩትን ሴቶች፣ እንዲሁም የከተማውን ታላላቅ ወንዶች ቀስቅሰው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደትን አስነሡ፤ ከአገራቸውም አስወጧቸው። ጳውሎስና በርናባስም ለማስጠንቀቂያ እንዲሆን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።
ሐዋርያት ሥራ 13 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 13:24-52
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች