እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉ ስለ ጠበቀው ንጉሥ ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ በሰላም ይኖር ነበር። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩ ናታንን “እነሆ እኔ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ቤት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል!” አለው። ናታንም “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ በልብህ ያሰብከውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት። ነገር ግን በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሂድና ለአገልጋዬ ለዳዊት እኔ ስለ እርሱ የምለውን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤተ መቅደስ የምትሠራልኝ አንተ ነህን? የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ በመታደግ ካዳንኩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ በድንኳን ውስጥ ሆኜ በየስፍራው ስዘዋወር ኖርኩ እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም፤ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው መሪዎች መካከል በሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቤት እንዲሠራልኝ የጠየቅሁት አለን?’ “ስለዚህም ለአገልጋዬ ለዳዊት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘እኔ አንተን የበግ መንጋ ከምትጠብቅበት መስክ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግኹህ፤ በሄድክበት ስፍራ ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርኩ፤ ወደፊትም በተራመድህ መጠን ጠላቶችህን ድል አደረግሁልህ፤ ገና ደግሞ በዓለም እንደ ታወቁት ታላላቅ መሪዎች ዝነኛ አደርግሃለሁ። ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ አዘጋጅቴ በራሳቸው ቦታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ለእነርሱ መሳፍንትን ከሾምኩበት ጊዜ ጀምሮ ክፉ አድራጊዎች ቀድሞ ያደርጉት እንደ ነበረው አያስጨንቋቸውም፤ አንተንም ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ከቤትህ አልጋህን የሚወርሱ ልጆች እተካልሃለሁ ብሎ ይገልጥልሃል።
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች