ጥቂት ዘግየት ብሎ ኢዮአብና ሌሎች የዳዊት ወታደሮች ብዙ ምርኮ ካገኙበት ዘመቻ ተመለሱ፤ ይሁን እንጂ አበኔር በዚያን ጊዜ ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ሄዶ ስለ ነበር በኬብሮን አልነበረም፤ ኢዮአብና ተከታዮቹ በደረሱም ጊዜ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሥ ዳዊት መጥቶ ንጉሡ አበኔርን በሰላም እንዳሰናበተው ለኢዮአብ ነገሩት። ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? አበኔር ወደ አንተ መጥቶ ሳለ እንዲሁ እንዲሄድ ያሰናበትከው ስለምንድን ነው? የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ እርሱ የመጣው አንተን አታሎ የምትወጣበትንና የምትገባበትን ለማየትና ምን እንደምታደርግ ለመሰለል ነው።” ኢዮአብ ከዳዊት ፊት ወጥቶ ከሄደ በኋላ አበኔርን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ከሲራ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ መልሰው አመጡለት፤ ዳዊት ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። አበኔር ወደ ኬብሮን በደረሰ ጊዜ ኢዮአብ በግል ሊያነጋግረው የፈለገ በመምሰል ወደ ቅጽሩ በር ገለል አድርጎ ወሰደው፤ እዚያም ሆዱን ወግቶ ገደለው፤ ኢዮአብ ይህን ያደረገበት ምክንያት አበኔር ቀደም ብሎ ወንድሙን ዐሣሄልን ስለ ገደለበት ለመበቀል ነው። ዳዊትም የአበኔርን መገደል በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔና በንጉሣዊ ግዛቴ ውስጥ ያለው ሕዝብ ስለ አበኔር መገደል ከደሙ ንጹሓን መሆናችንን እግዚአብሔር ያውቃል። ስለዚህም ቅጣቱ በኢዮአብና በቤተሰቡ ላይ ይውረድ! በዘመናት ሁሉ ከቤተሰቡ የአባለ ዘር ወይም የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው አይጥፋ! እንዲሁም አካለ ስንኩል የሆነ ሰው፥ በጦር ሜዳ የሚሞት ወይም የሚበላው አጥቶ የሚራብ ሰው አይታጣ!” በዚህ ዐይነት ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳይ ወንድማቸውን ዐሣሄልን በገባዖን በተደረገው ጦርነት ስለ ገደለ አበኔርን ገደሉት። ከዚህ በኋላ ዳዊት በሐዘን ልብሳቸውን ቀደው፥ ማቅ ለብሰው ለአበኔር እንዲያለቅሱ ኢዮአብንና የእርሱ ተከታዮች የሆኑትን ሰዎች አዘዘ፤ በቀብር ሥነ ሥርዓቱም ላይ ንጉሥ ዳዊት ራሱ አስክሬኑን ተከትሎ ሄደ፤ አበኔር በኬብሮን ተቀበረ፤ በመቃብሩም ላይ ንጉሡ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እርሱን በማየት በመረረ ሁኔታ አለቀሱ፤ ዳዊትም ለአበኔር ሐዘኑን በቅኔ ሲገልጥ እንዲህ አለ፦ “አበኔር እንደ ሞኝ ሰው ይሙትን? እጆችህ አልታሰሩም፤ እግሮችህ አልታበቱም፤ ታዲያ፥ በዚህ ሁኔታ ሳለ በወንጀለኞች እጅ እንደሚወድቅ ሰው እንዴት ተገደልክ!” ሕዝቡም ሁሉ ስለ እርሱ እንደገና አለቀሱ። ሰዎችም ቀኑን ሙሉ ዳዊት እህል ይቀምስ ዘንድ ለማግባባት ሞከሩ፤ እርሱ ግን “የዛሬይቱ ጀንበር ሳትጠልቅ እህል ብቀምስ እግዚአብሔር ይቅጣኝ!” ሲል ማለ። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ነገር ተመልክተው ደስ አላቸው፤ በእርግጥም ንጉሡ ያደረገው ነገር ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሰኛቸው። የዳዊት ሰዎችና መላው የእስራኤል ሕዝብ በአበኔር ሞት ንጉሥ ዳዊት ምንም ያልተባበረ መሆኑን ተገነዘቡ። ንጉሡም ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች እንዲህ አለ፤ “በዛሬው ቀን በእስራኤል ታላቅ መሪ እንደ ሞተ አታስተውሉምን? ምንም እንኳ እኔ እግዚአብሔር መርጦ የሾመኝ ንጉሥ ብሆን ዛሬ ደካማነት ተሰምቶኛል፤ እነዚህ የጸሩያ ልጆች በእኔ ላይ እጅግ የበረቱ ዐመፀኞች ሆነውብኛል፤ እነዚህን ነፍሰ ገዳዮች እግዚአብሔር ራሱ የሚገባቸውን ቅጣት ይስጣቸው!”
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3:22-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች