ዝነኞች የሆኑት የዳዊት ወታደሮች ስም ዝርዝር ከዚህ በታች እንደ ተመለከተው ነው፤ የመጀመሪያው የታሕክሞን ተወላጅ ዮሼብ ባሼቤት የተባለው ሲሆን እርሱም ከሦስቱ ኀያላን ብልጫ ያለው ተቀዳሚ ነው፤ ይህ ሰው በአንድ ውጊያ ላይ ጦሩን አንሥቶ ስምንት መቶ ኀያላን ሰዎችን ገደለ። ከሦስቱ ኀያላን ሁለተኛው ከአሖሕ ጐሣ የሆነው ዝነኛው የዶዶ ልጅ አልዓዛር ነበር፤ አንድ ቀን እርሱና ዳዊት ለጦርነት ተሰልፈው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያን ተገዳደሩ፤ እስራኤላውያን ወደ ኋላቸው አፈገፈጉ፤ ይህ ሰው ግን ባለበት ጸንቶ በመቆም እጁ ዝሎ በሰይፉ ላይ እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር ታላቅ ድልን አደረገ፤ ጦርነቱም ከቆመ በኋላ እስራኤላውያን አልዓዛር ወደነበረበት ስፍራ ተመልሰው ከሞቱት ፍልስጥኤማውያን ብዙ የጦር ልብስ ማረኩ። ከሦስቱ ኀያላን ሦስተኛው ደግሞ የሃራር ተወላጅ የሆነው ዝነኛው የአጌ ልጅ ሻማ ነበር፤ አንድ ቀን ፍልስጥኤማውያን የምስር ማሳ ባለበት በሌሒ ተሰልፈው ነበር፤ እስራኤላውያንም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሻማ ግን በዚያው በማሳው ውስጥ ጸንቶ ቆመ፤ በመከላከልም ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ ድልን አደረገ። በመከር ጊዜ መጀመሪያ ላይ ከሠላሳው ኀያላን በተለይ ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዐዱላም ዋሻ ወረዱ፤ ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ጥቂቱ ክፍል በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር፤ ዳዊት በዚያን ጊዜ በተመሸገ ኮረብታ ላይ ነበር፤ ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት አንድ ቡድን ቤተልሔምን በመውረር ያዘ፤ ዳዊትም አገሩን በመናፈቅ “በቤተልሔም ቅጽር በር አጠገብ ካለው የውሃ ጒድጓድ የምጠጣው ውሃ የሚያመጣልኝ ሰው ምነው ባገኘሁ!” አለ። ስለዚህ ዝነኞች የሆኑት ሦስቱ ኀያላን ወታደሮች የፍልስጥኤማውያንን ሰፈር በድፍረት ጥሰው በማለፍ ከጒድጓዱ ውሃ ቀድተው ለዳዊት ይዘውለት መጡ፤ ዳዊት ግን ሊጠጣ አልወደደም፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ ለእግዚአብሔር መባ አድርጎ ካፈሰሰው በኋላ፥ “እግዚአብሔር ሆይ! ይህን ውሃ ከቶ ልጠጣው አልችልም! እኔ እርሱን ብጠጣ፥ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ኀያላን ሰዎች ደም እንደ ጠጣሁ ይቈጠራል!” አለ፤ ውሃውንም መጠጣት እምቢ አለ። ዝነኞች የሆኑት ሦስቱ ኀያላን ወታደሮች የፈጸሙአቸው የጀግንነት ተግባሮች እነዚህ ናቸው። የጽሩያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ ዝነኞች የሆኑት የሠላሳዎቹ ወታደሮች አለቃ ነበር፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ ከሦስት መቶ ሰዎች ጋር በመዋጋት ሁሉንም ገደለ፤ ስለዚህም እንደ ሦስቱ ዝነኛ ሆነ። ከሠላሳዎቹ መካከል እጅግ ዝነኛ በመሆኑም የእነርሱ አለቃ ሆነ፤ ይሁን እንጂ የሦስቱን ጀግኖች ያኽል ዝነኛ አልነበረም። ሌላው ዝነኛ ወታደር የቃብጽኤል ተወላጅ የነበረው የዮዳሄ ልጅ በናያ ነበር፤ እርሱም ሁለት የታወቁ ሞአባውያን ወታደሮችን ከመግደሉም ሌላ ብዙ የጀግንነት ሥራ ፈጽሞአል፤ አንድ ጊዜ በምድር ላይ ዐመዳይ በወረደበት ቀን ወደ አንድ ዋሻ ወርዶ አንበሳ ገደለ፤ እንዲሁም ጦር ይዞ የነበረውን አንድ ኀያል ግብጻዊ ገድሎአል፤ ይኸውም በናያ በእጁ ከበትር በስተቀር ሌላ የጦር መሣሪያ ሳይዝ ወደ ግብጻዊው ቀርቦ የገዛ ጦሩን በመቀማት በዚያው ጦር ግብጻዊውን ገደለው። እንግዲህ እንደ ሦስቱ ኀያላን ዝነኛ የሆነው በናያ የፈጸማቸው የጀግንነት ሥራዎች እነዚህ ናቸው፤ ከሠላሳዎቹ መካከል እጅግ ታዋቂ ቢሆንም በዝነኛነቱ ከሦስቱ ኀያላን ደረጃ አልደረሰም፤ ዳዊትም በናያን የክብር ዘቡ አዛዥ አድርጎ ሾሞት ነበር። ከሠላሳዎቹ መካከል የሌሎቹ ሰዎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ የኢዮአብ ወንድም ዐሣሄል፤ የቤተልሔሙ ተወላጅ የዶዶ ልጅ ኤልሐናን፤ የሐሮድ ተወላጆች የሆኑት ሻማና ኤሊቃ፤ የፌሌጥ ተወላጅ የሆነው ሔሌጽ፤ የተቆዓ ተወላጅ የሆነው የዒቄሽ ልጅ ዒራ፤ የዐናቶት ተወላጅ የሆነው አቢዔዜር፤ የሑሻ ተወላጅ የሆነው መቡናይ፤ የአሖሕ ተወላጅ የሆነው ጻልሞን፤ የነጦፋ ተወላጅ የሆነው ማህራይ፤ የነጦፋ ተወላጅ የሆነው የባዕና ልጅ ሔሌብ፤ በብንያም ግዛት የምትገኘው የጊብዓ ተወላጅ የሆነው የሪባይ ልጅ ኢታይ፤ የፒርዓቶን ተወላጅ የሆነው በናያ፤ በጋዓሽ ሸለቆ አጠገብ የተወለደው ሂዳይ፤ የዓርባ ተወላጅ የሆነው ኢቢዓልቦን፤ የባርሑም ተወላጅ የሆነው ዓዝማዌት፤ የሻዓልቦን ተወላጅ የሆነው ኤልያሕባ፤ የያሼን ልጆች፤ ዮናትን፤ የሐራር ተወላጅ የሆነው ሻማ፤ የሐራር ተወላጅ የሆነው የሻራር ልጅ አሒአም፤ የማዕካ ተወላጅ የሆነው የአሐሰባይ ልጅ ኤሊፌሌጥ፤ የጊሎ ተወላጅ የሆነው የአኪጦፌል ልጅ ኤሊዓም፤ የቀርሜሎስ ተወላጅ የሆነው ሔጽሮ፤ የዐረብ ተወላጅ የሆነው ፓዓራይ፤ የጾባ ልጅ የሆነው የናታን ልጅ ዪግአል የጋድ ተወላጅ የሆነው ባኒ፤ የዐሞን ተወላጅ የሆነው ጼሌቅ፤ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ የነበረውና የበኤሮት ተወላጅ የሆነው ናሕራይ፤ የያቲር ተወላጆች የሆኑት ዒራና ጋሬብ፤ ሒታዊው ኦርዮን። ዝነኞች የሆኑት ኀያላን ወታደሮች ጠቅላላ ድምር ሠላሳ ሰባት ነበር።
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 23:8-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች