ንጉሥ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም ሞት በብርቱ አዝኖ በማልቀስ ላይ መሆኑን ኢዮአብ ሰማ፤ እንዲሁም ንጉሡ በልጁ ሞት ምክንያት በሐዘን ላይ መሆኑን ስለ ሰሙ ወታደሮቹ ያገኙት የድል አድራጊነት ደስታ በዚያ ቀን ወደ ሐዘን ተለወጠባቸው። ስለዚህ ከጦር ግንባር ተመልሰው ወደ ኋላ እንደሚሸሹ ወታደሮች ድምፃቸውን አጥፍተው በጸጥታ ወደ ከተማይቱ ገቡ፤ ንጉሡም ፊቱን ሸፍኖ “ልጄ ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! አቤሴሎም ልጄ!” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያለቅስ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የቊባቶችህን ሕይወት ያዳኑትን ሰዎች ዛሬ አሳፍረሃቸዋል፤ አንተ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የሚጠሉህን ግን ትወዳለህ! ስለ ጦር መኰንኖችህና ስለ ወታደሮችህ ሁሉ ምንም የማይገድህ መሆኑን በግልጥ አሳይተሃል፤ አቤሴሎም በሕይወት ቢኖርና እኛ ሁላችን ብንጠፋ ኖሮ እጅግ እንደምትደሰት ተገንዝቤአለሁ፤ ይልቅስ አሁን ተነሥና ወታደሮችህን አበረታታ፤ ይህንን ባታደርግ ግን ነገ ጠዋት ከእነርሱ አንዱ እንኳ ከአንተ ጋር እንደማይሆን በእግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ይህም በሕይወትህ ከደረሰብህ መከራ ሁሉ እጅግ የከፋ ይሆንብሃል።” ከዚህ በኋላ ንጉሡ ከተቀመጠበት ተነሥቶ በመሄድ በከተማይቱ ቅጽር በር አጠገብ ተቀመጠ፤ ተከታዮቹም እዚያ መሆኑን ሰምተው ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ። በዚህን ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ ሸሽተው እያንዳንዱ ወደየቤቱ ሄዶ ነበር፤ በመላ አገሪቱም ሕዝቡ እርስ በርስ መጣላት ጀመረ፤ እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ንጉሥ ዳዊት ከጠላቶቻችን እጅ አድኖናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አውጥቶናል፤ አሁን ግን ከአቤሴሎም ፊት በመሸሽ አገሪቱን ትቶ ሄዶአል። መሪያችን ይሆን ዘንድ አቤሴሎምን ቀብተን አንግሠነው ነበር፤ ነገር ግን እርሱ በጦርነት ላይ ተገደለ፤ ታዲያ፥ ንጉሥ ዳዊትን መልሶ ለማምጣት የሚሞክር ሰው እንዴት ታጣ?” ንጉሥ ዳዊትም እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው የተናገሩትን ሰማ፤ ስለዚህም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን በመላክ የይሁዳን መሪዎች እንዲህ ብለው እንዲጠይቁአቸው አዘዘ፤ “ንጉሡን ረድታችሁ ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ ስለምን እናንተ የመጨረሻዎቹ ትሆናላችሁ? እናንተ እኮ ለእኔ የሥጋ ዘመዶቼ ናችሁ፤ ታዲያ፥ እኔን መልሶ ለመውሰድ የመጀመሪያዎቹ በመሆን ፈንታ ስለምን የመጨረሻዎቹ ትሆናላችሁ?” እንዲሁም ለዐማሳ ሲናገር “አንተም ለእኔ የሥጋ ዘመድ ነህ፤ ከአሁን ጀምሮ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ አደርግሃለሁ፤ ይህንንም ባላደርግ እግዚአብሔር በሞት ይቅጣኝ!” ብላችሁ ንገሩት ሲል አዘዛቸው። የዳዊት አነጋገር የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ለእርሱ ታማኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው፤ ስለዚህም ከመኳንንቱ ሁሉ ጋር ተመልሶ እንዲመጣ ላኩበት። ዳዊት በመመለስ ላይ እንዳለም የይሁዳ ሰዎች እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ሄደው ተቀበሉት፤ አጅበውም ወንዙን ለማሻገር አስበው እስከ ጌልጌላ ድረስ መጡ፤ በዚያኑ ጊዜም የባሑሪም ተወላጅ የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሺምዒ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ፈጥኖ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር የብንያም ነገድ የሆኑ አንድ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ የሳኦል ቤተሰብ አገልጋይ የነበረው ጺባም ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከኻያ አገልጋዮቹ ጋር መጣ፤ ወደ ዮርዳኖስም ወንዝ እየተጣደፉ ደርሰው በንጉሡ ፊት ቀረቡ። እነርሱም ንጉሡንና ተከታዮቹን በጀልባ አጅበው ወደ ማዶ ለማድረስና ንጉሡ የሚፈልገውን ሁሉ ለማድረግ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ። ንጉሡ ወንዙን ለመሻገር ሲዘጋጅ ሳለ የጌራ ልጅ ሺምዒ መጥቶ በፊቱ ተዘረጋና እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ሆይ! ከኢየሩሳሌም ወጥተህ በሄድክበት ቀን ያደረግኹትን በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ ቂም በቀልም አትያዝብኝ፤ ዳግመኛም ስለ እርሱ አታስብ፤ ጌታዬ ሆይ! ኃጢአት እንደ ሠራሁ ዐውቃለሁ፤ ዛሬ ግን ከሰሜን የእስራኤል ነገዶች የመጀመሪያው በመሆን አንተን ለመቀበል መጥቼአለሁ።” የጸሩያ ልጅ አቢሳም “እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠውን ስለተሳደበ ሺምዒ በሞት መቀጣት ይገባዋል” ሲል ተናገረ። ዳዊት ግን አቢሳንና ወንድሙን ኢዮአብን “ይህን አሳብ እንድታቀርቡ የጠየቃችሁ ማን ነው? ችግር ልታመጡብኝ ትፈልጋላችሁን? እነሆ፥ አሁን የእስራኤል ንጉሥ እኔ ነኝ፤ ደግሞም በዛሬው ዕለት ማንም እስራኤላዊ በሞት አይቀጣም” አላቸው። ሺምዒንም “በሞት እንደማትቀጣ ቃል እገባልሃለሁ!” አለው።
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች