የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞአብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። በዚህም ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ በሰማርያ ቤተ መንግሥቱ ሳለ ከሰገነቱ ላይ ወድቆ በብርቱ ስለ ቈሰለ ታሞ ነበር፤ እርሱም “እኔ ከዚህ ሕመም እድን ወይም አልድን እንደ ሆነ በፍልስጥኤም የዔክሮን ከተማ አምላክ የሆነውን ብዔልዜቡልን ጠይቃችሁልኝ ኑ” ብሎ መልእክተኞቹን ላከ። ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ተነሥተህ የሰማርያ ንጉሥ አካዝያስ የላካቸውን መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣ፤ እንዲህም ብለህ ንገራቸው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱት፥ በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብላችሁ በማሰብ ነውን?’ ስለዚህም እግዚአብሔር፥ ‘እነሆ አንተ ትሞታለህ እንጂ አትፈወስም! ከተኛህበት አልጋም አትነሣም! ብሎሃል’ በሉት።” ስለዚህ ኤልያስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ መልእክተኞቹም ወደ ንጉሡ ተመልሰው ሄዱ፤ ንጉሡም “ስለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንድ ሰው በመንገድ አግኝቶን ወደ አንተ ተመልሰን እንድንመጣና እግዚአብሔር ስለ አንተ የተናገረውን እንድናስረዳህ አዘዘን፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክህበት ምክንያት ምንድን ነው? በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብለህ በማሰብህ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከዚህ ሕመም አትፈወስም! ከተኛህበትም አልጋ አትነሣም!’ ” ንጉሡም “በመንገድ ያገኛችሁትና ይህን ቃል የነገራችሁ ያ ሰው እንዴት ያለ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ጠጒራም ልብስ ለብሶ በወገቡ ዙሪያ የጠፍር ቀበቶ የታጠቀ ነው” ሲሉ መለሱለት። ንጉሡም “እርሱማ ኤልያስ ነው!” አለ። ከዚህም በኋላ ንጉሡ አንዱን የጦር መኰንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሄዶ ኤልያስን ይዞ ያመጣለት ዘንድ አዘዘው፤ መኰንኑም ኤልያስን በአንድ ኰረብታ ላይ ተቀምጦ አገኘውና “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው። ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ!” አለው፤ በዚያም ጊዜ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ መኰንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ። ንጉሡም እንደገና ሌላውን መኰንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ላከ፤ እርሱም ወደ ኤልያስ ወጥቶ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! አሁኑኑ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል!” አለው። ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ!” አለው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር እሳት መኰንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ። ንጉሡም ለሦስተኛ ጊዜ ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሌላ መኰንን ላከ፤ ይህኛው መኰንን ግን ወደ ኰረብታው በመውጣት በኤልያስ ፊት በጒልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት ሰዎች ምሕረት አድርግልን! ሕይወታችንንም ከሞት አድን! ሌሎቹን ሁለት መኰንኖችና ተከታዮቻቸውን ሁሉ ከሰማይ የወረደ እሳት በልቶአቸዋል፤ ለእኔ ግን እባክህ ምሕረት አድርግልኝ!” በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ኤልያስን “ከእርሱ ጋር አብረህ ውረድ፤ ከቶም አትፍራ” አለው። ስለዚህም ኤልያስ ከመኰንኑ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ፤
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 1:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች