2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:3-11

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:3-11 አማ05

ለምሕረት አባትና መጽናናትን ሁሉ ለሚሰጥ እንዲሁም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አባት ለእግዚአብሔር፥ ምስጋና ይሁን። እኛ ከእግዚአብሔር በምናገኘው መጽናናት በመከራ ላይ ያሉትን ሁሉ ማጽናናት እንድንችል እግዚአብሔር እኛን በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል። የክርስቶስን መከራ በብዛት እንደ መካፈላችን መጠን እንዲሁም በክርስቶስ መጽናናትን በብዛት እናገኛለን። እኛ መከራ ስንቀበል እናንተ መጽናናትንና መዳንን ታገኛላችሁ፤ እኛ ስንጽናና ደግሞ እናንተም እኛ የምንቀበለውን ዐይነት መከራ በትዕግሥት ተቀብላችሁ ትጽናናላችሁ፤ መከራችንን በምትካፈሉበት መጠን መጽናናታችንንም እንደምትካፈሉ ስለምናውቅ በእናንተ ላይ ያለን ተስፋ ጽኑ ነው። ወንድሞች ሆይ! በእስያ ክፍለ ሀገር በነበርንበት ጊዜ የደረሰብንን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ ይህም የደረሰብን መከራ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ወድቆብን ስለ ነበር በሕይወት ለመኖር የነበረን ተስፋ እንኳ ተቋርጦ ነበር። እንዲያውም ሞት እንደ ተፈረደብን ያኽል ተሰምቶን ነበር፤ ይህም ሁሉ የደረሰብን፥ የምንተማመነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ኀይል አለመሆኑን እንድንገነዘብ ነው። ስለዚህ እርሱ ለሞት ከሚያደርስ አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ደግሞም እንደሚያድነን ተስፋችን በእርሱ ነው። እናንተም እኛን በጸሎት ልትረዱን ይገባል፤ በብዙ ጸሎት እኛ የእግዚአብሔርን ርዳታ ስናገኝ ብዙ ሰዎች ደግሞ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ።