ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 25

25
የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ
(2ነገ. 14፥2-6)
1አሜስያስ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ሲሆን ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱ ይሆዓዲን ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች፤ 2አሜስያስ አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር ያደርግ ነበር፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የሚያደርገውን ነገር በሙሉ ልብ አያደርግም ነበር፤ 3መንግሥቱን እንዳጠናከረ ወዲያውኑ አባቱን የገደሉትን ባለሥልጣኖች በሙሉ በሞት ቀጣ፤ 4ይሁን እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም፤ ልጆቻቸውንም ያልገደለበት ምክንያት እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ሕግ “ወላጆች ልጆቻቸው በፈጸሙት ወንጀል፥ ልጆችም ወላጆቻቸው በፈጸሙት ወንጀል በሞት አይቀጡም፤ አንድ ሰው በሞት መቀጣት ያለበት ራሱ በፈጸመው ወንጀል ብቻ ነው” ሲል የተናገረውን ቃል በማክበር ነው። #ዘዳ. 24፥16።
በኤዶም ላይ የተደረገ ጦርነት
(2ነገ. 14፥7)
5ንጉሥ አሜስያስ የይሁዳና የብንያም ነገዶች የሆኑትን ወንዶች ሁሉ በየጐሣዎቻቸው በቡድን በቡድን በመደልደል በየቡድኑ በሺህ አለቆችና በመቶ አለቆች ሥር መደበ፤ በቡድን የተመደቡትም ሰዎች ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶችን ሁሉ የሚያጠቃልል ሲሆን ብዛታቸውም ሦስት መቶ ሺህ ነበር፤ እነርሱም ለጦርነት የተዘጋጁ፥ በጦርና በጋሻ አያያዝ የሠለጠኑ ምርጥ ወታደሮች ነበሩ፤ 6አሜስያስ በተጨማሪ በሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ጥሬ ብር ከእስራኤል አንድ መቶ ሺህ ወታደሮችን ቀጠረ፤ 7ነገር ግን አንድ ነቢይ ወደ ንጉሥ አሜስያስ መጥቶ “እግዚአብሔር ከኤፍሬምም ሆነ ከማንኛውም የእስራኤል ሕዝብ ጋር ስላልሆነ እነዚህን የእስራኤል ወታደሮች ይዘህ አትዝመት” አለው። 8“አንተ በዚህ በምታደርገው ጦርነት የእስራኤል ወታደሮች ድጋፍ ይሆኑኛል ብለህ ታስብ ይሆናል፤ ነገር ግን አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ እንድትሆን የሚያደርግህ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እነሆ አሁንም እርሱ በጠላቶችህ ድል እንድትሆን ያደርግሃል።”
9አሜስያስ፥ ነቢዩን “አስቀድሜ የከፈልኩትስ ያ ሁሉ ገንዘብ እንዴት ሊሆን ነው?” ሲል ጠየቀው።
ነቢዩም “እግዚአብሔር ከዚህ ገንዘብ ይበልጥ የበዛ ሊሰጥህ ይችላል!” ሲል መለሰለት። 10ስለዚህ አሜስያስ ቅጥረኞቹን ወታደሮች ወደየመኖሪያ ስፍራቸው እንዲሄዱ አሰናበታቸው፤ እነርሱም በይሁዳ ሕዝብ ላይ እጅግ ተቈጥተው ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ሄዱ።
11ከዚህ በኋላ አሜስያስ በወኔ ተነሣሥቶ ወታደሮቹን በመምራት ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፤ በዚያም ወታደሮቹ በኤዶም ሠራዊት ላይ አደጋ ጥለው ዐሥር ሺህ ወታደሮችን ገደሉ፤ 12ሌሎች ዐሥር ሺህ ወታደሮችንም ማረኩ፤ እስረኞቹንም ሴላዕ ተብላ በምትጠራው ከተማ አጠገብ በሚገኘው ገደል አፋፍ ላይ አውጥተው ጣሉአቸው፤ ሁሉም ከገደሉ በታች በሚገኙ አለቶች ላይ ተፈጥፍጠው ሞቱ።
13በዚሁ ወቅት፥ አሜስያስ ከእርሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዲሄዱ ያልፈቀደላቸው የእስራኤል ወታደሮች በሰማርያና በቤትሖሮን መካከል በሚገኙት በይሁዳ ከተማዎች ላይ አደጋ በመጣል ሦስት ሺህ ሰዎችን ገደሉ፤ እጅግ የበዛ ምርኮም ወሰዱ።
14አሜስያስ ኤዶማውያንን ድል አድርጎ በተመለሰ ጊዜ ጣዖቶቻቸውን ይዞ መጣ፤ አማልክት አድርጎም በማቆም ሰገደላቸው፤ ዕጣንም አጠነላቸው፤ 15ይህም ድርጊት እግዚአብሔርን አስቈጣ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ አሜስያስ አንድ ነቢይ ላከ፤ ይህም ነቢይ አሜስያስን “የገዛ ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ለማዳን እንኳ ላልቻሉ ለባዕዳን አማልክት ስለምን ሰገድክ?” ሲል ጠየቀው።
16ነቢዩ ገና ንግግሩን ሳይፈጽም አሜስያስ “ለመሆኑ አንተን የንጉሡ አማካሪ አድርገን የሾምንህ ከመቼ ወዲህ ነው? ይልቅስ ንግግርህን አቁም፤ አለበለዚያ እገድልሃለሁ!” አለው።
ነቢዩም ለአንድ አፍታ ንግግሩን ቆም ካደረገ በኋላ “ይህን ሁሉ በማድረግህና የእኔን ምክር ለመስማት እምቢ በማለትህ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ መወሰኑን አሁን ዐወቅሁ” አለው።
በእስራኤል ላይ የተደረገ ጦርነት
(2ነገ. 14፥8-20)
17ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሜስያስና አማካሪዎቹ በእስራኤል ላይ አሤሩ፤ አሜስያስም የኢዩ የልጅ ልጅ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ዮአስ መልእክተኞች በመላክ “እንግዲህ፥ ና ይዋጣልን?” ሲል ለጦርነት አነሣሣው፤ 18ንጉሥ ዮአስ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንድ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ላይ የምትገኝ ኲርንችት ወደ ሊባኖስ ዛፍ መልእክት ልካ ‘ለወንድ ልጄ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሴት ልጅህን ስጠኝ’ ስትል ጠየቀችው፤ ነገር ግን አንድ አውሬ በዚያ በኩል ሲያልፍ ስለ ረገጣት ያቺ ኲርንችት ሞተች፤ 19አሜስያስ ሆይ፥ እነሆ አንተም ኤዶማውያንን ድል ስላደረግህ ልብህ በትዕቢት ተሞልቶአል፤ ይልቅስ በቤትህ ዐርፈህ ብትቀመጥ የሚሻልህ መሆኑን እመክርሃለሁ፤ በአንተና በሕዝብህ ላይ መቅሠፍትን የሚያስከትል ነገር ለመቈስቈስ ስለምን ትፈልጋለህ?”
20አሜስያስ ግን የዮአስን ምክር ከምንም አልቈጠረውም፥ ይህም የሆነበት ምክንያት አሜስያስ የኤዶማውያንን ጣዖቶች ስላመለከ ድል እንዲሆን እግዚአብሔር ስለ ፈቀደ ነው፤ 21ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ለመውጋት ዘመተ፤ በይሁዳ በሚገኘው ቤትሼሜሽ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ጦርነት ገጠሙ፤ 22የይሁዳ ሠራዊትም ድል ሆነ፤ ወታደሮቹም ሸሽተው ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ሄዱ፤ 23ንጉሥ ዮአስም አሜስያስን ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ ከኤፍሬም ቅጽር በር አንሥቶ እስከ ማእዘን ቅጽር በር ድረስ ያለውን ርዝመቱ ሁለት መቶ ሜትር ያኽል የሆነውን የኢየሩሳሌምን ቅጽር አፈረሰ። 24በቤተ መቅደስ የነበረውን ወርቅና ብር ሁሉ፥ በዖቤድኤዶም ዘሮች ይጠበቁ የነበሩትን የቤተ መቅደሱን ዕቃዎችና የቤተ መንግሥቱን ሀብት በሙሉ ምርኮ አድርጎ በመያዣም ስም የወሰዳቸውን ሰዎች በመውሰድ ወደ ሰማርያ ይዞ ሄደ።
የአሜስያስ መሞት
25የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ከሞተ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ፤ 26አሜስያስ በዘመነ መንግሥቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 27አሜስያስ እግዚአብሔርን ከተወበት ጊዜ ጀምሮ በኢየሩሳሌም ውስጥ እርሱን ለመግደል ሤራ ተጠንስሶ ነበር፤ በመጨረሻም አሜስያስ ሸሽቶ ወደ ላኪሽ ሄደ፤ ነገር ግን ጠላቶቹ እዚያው ድረስ ልከው አስገደሉት፤ 28ሬሳውንም በፈረስ ላይ ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ