ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 24

24
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ
(2ነገ. 12፥1-16)
1ኢዮአስ በሰባት ዓመቱ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ጺቢያ ተብላ የምትጠራ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች፤ 2ካህኑ ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ ኢዮአስ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያስኝ ነገር ያደርግ ነበር፤ 3ዮዳሄ ለንጉሥ ኢዮአስ ሁለት ሚስቶችን መርጦለት ነበር፤ እነርሱም ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወልደውለታል።
4ኢዮአስ ከነገሠ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤተ መቅደሱን ለማደስ ወሰነ፤ 5ስለዚህ ካህናቱንና ሌዋውያኑን በአንድነት ሰብስቦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ ለአምላካችሁ ቤት ዓመታዊ እድሳት የሚሆን በቂ ገንዘብ ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በፍጥነት ሰብስቡ” ሲል አዘዛቸው፤ ሌዋውያኑ ግን ቸል በማለት ዘገዩ፤ 6ስለዚህ ንጉሥ ኢዮአስ የሌዋውያኑን መሪ ዮዳሄን ጠርቶ፦ “የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ፥ እግዚአብሔር ለሚመለክበት ድንኳን አገልግሎት የሚሆን ግብር የእስራኤል ሕዝብ እንዲያዋጣ ያዘዘውን ሌዋውያኑ ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሰብስበው ያመጡ ዘንድ ስለምን አላተጋሃቸውም?” አለ። #ዘፀ. 30፥11-16።
7የዚያች ዐታልያ ተብላ የምትጠራ ክፉይቱ ሴት ተከታዮች ቤተ መቅደሱን አበላሽተውት ነበር፤ ንዋያተ ቅድሳቱን እንኳ ሳይቀር ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት በሚደረገው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ይጠቀሙባቸው ነበር።
8ንጉሥ ኢዮአስ “የገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ሠርታችሁ በቤተ መቅደሱ ቅጽር በር በስተውጭ በኩል አኑሩት” ሲል ሌዋውያኑን አዘዘ፤ 9ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በመላው ኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚገኙ ነዋሪዎች ሁሉ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእስራኤል ሕዝብ እንዲሰበሰብ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር እንዲያመጡ ትእዛዝ አስተላለፉ፤ 10ይህም ሕዝቡንና መሪዎቹን ሁሉ ደስ ስላሰኛቸው ገንዘብ በማምጣት ሣጥኑን ሞሉት። 11ሌዋውያኑም ሣጥኑን ወስደው ኀላፊዎች ለሆኑት ለመንግሥት ባለሥልጣኖች በየቀኑ ያስረክቡት ነበር። ሣጥኑ በገንዘብ በሞላ ቊጥር የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊና የካህናት አለቃው እንደ ራሴ ገንዘቡን ከሣጥኑ አውጥተው ከወሰዱ በኋላ፥ ሣጥኑን መልሰው በቦታው ያኖሩት ነበር፤ በዚህ ዐይነት ብዙ ገንዘብ ሰበሰቡ።
12ንጉሡና ካህኑ ዮዳሄ ገንዘቡን የቤተ መቅደሱ እድሳት ኀላፊዎች ለሆኑት ሰዎች ይሰጡአቸው ነበር፤ እነዚህም ኀላፊዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን የሚጠግኑ ግንበኞችን፥ አናጢዎችንና ብረታ ብረት ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር፤ 13ሠራተኞቹም በብርቱ ትጋት በመሥራት ቤተ መቅደሱን ቀድሞ በነበረው ሁኔታ በጥሩ አኳኋን አደሱት። 14የእድሳቱ ሥራ ባለቀ ጊዜም ቀሪው ገንዘብ ለንጉሥ ኢዮአስና ለካህኑ ዮዳሄ ተሰጠ፤ እነርሱም በዚህ ወርቅ ለቤተ መቅደሱ አገልግሎትና ለመሥዋዕት የሚውሉ ሳሕኖችንና ሌሎች ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ገዙ።
የዮዳሄ አመራር ተለወጠ
ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ ዘወትር በቤተ መቅደስ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር፤ 15ዮዳሄ በዕድሜ እጅግ ከሸመገለ በኋላ በአንድ መቶ ሠላሳ ዓመቱ ሞተ፤ 16እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ፥ ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ ስለ ሰጠው አገልግሎት ውለታ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት።
17ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ግን የይሁዳ መሪዎች ወደ ንጉሥ ኢዮአስ መጥተው እጅ በመንሣት ፍላጎታቸውን ገለጡለት፤ እርሱም በሐሳቡ ተስማማ፤ 18ስለዚህ ሰዎቹም በቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ መስገድ ትተው፥ አሼራ ተብላ ለምትጠራ ሴት አምላክ ጣዖቶችና ምስሎች መስገድ ጀመሩ። ይህንንም ኃጢአት በመሥራታቸው የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ። 19እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንዲመለሱ አጥብቀው ያሳስቡአቸው ዘንድ ነቢያትን ላከ፤ መሰከሩባቸውም፤ እነርሱ ግን አላዳመጡም፤ 20ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ ወረደ፤ እርሱም ሕዝቡ ሊያዩት በሚችሉበት ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ቆሞ “እግዚአብሔር ‘ትእዛዞቼን ስለምን ትተላለፋላችሁ? በገዛ ራሳችሁስ ላይ ስለምን ጥፋትን ታመጣላችሁ?’ ሲል ይጠይቃችኋል፤ እንግዲህ እናንተ ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቶአችኋል” አላቸው። 21ንጉሥ ኢዮአስ በዘካርያስ ላይ በተደረገው ሤራ ተባባሪ ሆነ፤ ሕዝቡም በንጉሡ ትእዛዝ ዘካርያስን በቤተ መቅደሱ አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። #ማቴ. 23፥35፤ ሉቃ. 11፥51። 22ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቅን አገልግሎት በመዘንጋት ዘካርያስን ገደለ፤ ዘካርያስም ሊሞት ሲያጣጥር ሳለ “እግዚአብሔር ይህን ግፍ ተመልክቶ ይቅጣህ” አለ።
የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
23በዚያን ዓመት በመከር ወራት የሶርያ ወታደሮች በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል መሪዎቹን ሁሉ ገደሉ፤ እጅግ ብዙ የሆነ ምርኮም ይዘው ወደ ደማስቆ ተመለሱ፤ 24የሶርያ ሠራዊት ቊጥር ጥቂት ነበር፤ ነገር ግን እጅግ ብዙ የሆነውን የይሁዳን ሠራዊት ድል እንዲያደርግ እግዚአብሔር ፈቀደ፤ ይህም የሆነው እነርሱ የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተዉ ነው፤ በዚህ ዐይነት በኢዮአስ ላይ ትክክለኛ ፍርድ ተፈጸመበት። 25በብርቱም ቈስሎ ነበር፤ የጠላት ሠራዊት ከዚያ ተነሥቶ ከሄደ በኋላ ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለሥልጣኖች የካህኑን የዮዳሄን ልጅ ደም ለመበቀል በንጉሡ ላይ አሢረው በአልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት፤ ንጉሡም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ይሁን እንጂ በነገሥታት መካነ መቃብር አልተቀበረም። 26በንጉሡ ላይ ያሤሩትም ሺምዓት ተብላ የምትጠራ የዐሞን ተወላጅ ልጅ የሆነው ዛባድና ሺምሪት ተብላ የምትጠራ የሞአብ ተወላጅ ልጅ የሆነው ይሆዛባድ ናቸው። 27የኢዮአስ ልጆች ታሪክ፥ በኢዮአስ ላይ ተነግረው የነበሩት የትንቢት ቃላትና ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን እንዴት እንዳደሰ በነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ መግለጫ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ