አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18:6-16

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18:6-16 አማ05

ዳዊት ጎልያድን ገድሎ ሲመለስና ወታደሮችም ወደየቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ፥ በእስራኤል በሚገኙት ከተሞች ሁሉ የሚኖሩ ሴቶች ሳኦልን ለመቀበል ወጡ፤ እነርሱም በእልልታ እየዘፈኑና እየጨፈሩ፥ የመስንቆ ድምፅ እያሰሙ አታሞ ይመቱ ነበር። ሴቶቹም ባደረጉት የአቀባበል ሥርዓት ላይ “ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ ገዳይ!” እያሉ ዘፈኑ። ሳኦል ይህ አባባል ደስ ስላላሰኘው በጣም ተቈጥቶ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ፥ ለእኔ ግን አንድ ሺህ ብቻ ሰጡ፤ እንግዲህ ከመንገሥ በቀር ምን ቀረው!” አለ። ከዚህም የተነሣ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ ቅናትና ጥርጣሬ አደረበት። በማግስቱም በድንገት ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቈራኘው፤ በቤቱም ውስጥ እንደ እብድ ይለፈልፍ ነበር፤ ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ በነበረው ዐይነት ለሳኦል በገና ይደረድርለት ነበር፤ ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። “መትቼ ከግድግዳ ጋር አጣብቀዋለሁ!” ብሎ በልቡ አሰበ፤ ከዚህም በኋላ ጦሩን በዳዊት ላይ ሁለት ጊዜ ወረወረ፤ ዳዊት ግን ሁለቴም ዞር እያለ አመለጠ። እግዚአብሔር እርሱን ትቶ ከዳዊት ጋር ስለ ነበረ ሳኦል ዳዊትን ፈራው፤ ከዚህም የተነሣ ሳኦል ዳዊትን ከፊቱ ለማራቅ የሺህ ወታደሮች አዛዥ አድርጎ ላከው፤ ዳዊትም ወታደሮቹን ወደ ጦርነት መራ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። ሳኦልም የዳዊትን ተልእኮ መሳካት እየተመለከተ በይበልጥ ይፈራው ጀመር፤ ነገር ግን ተልእኮው የሚሳካለት መሪ በመሆኑ በእስራኤልም ሆነ በይሁዳ የሚገኝ ሕዝብ ሁሉ ዳዊትን ይወድ ነበር፤