አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን የጦር መሣሪያ የሚሸከምለትን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን “ወደ ፍልስጥኤማውያን የጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ነገር ግን ዮናታን ይህን ጉዳይ ለአባቱ እንኳ አልነገረውም፤ በዚህ ጊዜ ሳኦል ከጊብዓ በጣም ሳይርቅ በሚግሮን በአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ከእርሱም ጋር ስድስት መቶ ያኽል ጭፍሮች ነበሩ፤ በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ ካህኑ ፊንሐስ የወለደው የኢካቦድ ወንድም የአሒጡብ ልጅ አኪያ ኤፉድ ለብሶ ከእርሱ ጋር አብሮ ነበር። እነርሱም ዮናታን ወዴት እንደ ሄደ አላወቁም ነበር። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ለመድረስ በሚክማስ መተላለፊያ መውጣት ነበረበት፤ በመተላለፊያውም ከግራና ከቀኝ ሁለት ሾጣጣ አለቶች ሲኖሩ የአንደኛው አለት ስም ቦጼጽ፥ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ተብሎ ይጠራል፤ ከአለቶቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር። ዮናታን ጋሻ ጃግሬ የሆነውን ወጣት “ና ወደ እነዚያ ወደ አልተገረዙት ወገኖች የጦር ሰፈር እንሻገር እግዚአብሔር ይረዳን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት እግዚአብሔር ማዳን አይሳነውም” አለው። ወጣቱም ጋሻጃግሬ “የምትፈቅደውን ነገር ሁሉ አድርግ፤ እኔ ከአንተ አልለይም፤ በሙሉ ልቤም ከአንተ ጋር ነኝ” አለው። ዮናታንም እንዲህ አለው፤ “እሺ እንግዲያውስ ወደ ማዶ እንሻገርና ለፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት እንታያቸው፤ እነርሱም ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ በዚያ ጠብቁን’ ቢሉን፥ ባለንበት እንቈያለን፤ ነገር ግን ‘ወደ እኛ ኑ’ ቢሉን፥ ወደ እነርሱ እንሄዳለን፤ ይህም እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን የሚያቀዳጀን ለመሆኑ ምልክት ይሆንልናል።” እነርሱም ወጣ ብለው ለፍልስጥኤማውያን ታዩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም “እነሆ! አንዳንድ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጒድጓድ በመውጣት ላይ ናቸው!” ተባባሉ፤ ከዚህ በኋላ ፍልስጥኤማውያን ዮናታንንና ጋሻጃግሬውን ጠርተው “የምንነግራችሁ ጉዳይ ስላለን ወደዚህ እኛ ወዳለንበት ኑ!” አሉአቸው። ዮናታንም ጋሻጃግሬውን “እንግዲህ ተከተለኝ፤ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን ለእስራኤል ይሰጣል” አለው፤ ዮናታንም በእጁና በጒልበቱ እየዳኸ ወደ አፋፉ ወጣ፤ ጋሻጃግሬውም ተከተለው፤ ዮናታንም በፍልስጥኤማውያን ላይ ድንገተኛ አደጋ በመጣል መታቸው፤ ጋሻጃግሬውም ገደላቸው። በመጀመሪያውም ግድያ በአንድ የእርሻ ክልል ላይ ኻያ ያኽል ሰዎችን ገደሉ፤ በገጠር የነበሩ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ተሸበሩ፤ አደጋ ጣዮችና በሰፈር የነበሩ ወታደሮችም ሁሉ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ እግዚአብሔር በላከባቸውም አስጨናቂ ሽብር መሬት ተንቀጠቀጠች። የሳኦል ወታደሮች የብንያም ግዛት በሆነችው በጊብዓ መሽገው ሁኔታውን ሁሉ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በመታወክ የሚሸሹትን ፍልስጥኤማውያን አዩ። ስለዚህም ሳኦል “እስቲ ወታደሮችን ቊጠሩና ከእኛ መካከል የጐደሉ እንዳሉ አረጋግጡ” ብሎ አዘዘ፤ በትእዛዙም መሠረት ሠራዊቱን በቈጠሩ ጊዜ ዮናታንና ጋሻጃግሬው አለመኖራቸው ታወቀ። ሳኦልም ካህኑን አኪያን “ኤፉዱን ይዘህ ና” አለው። በዚያን ቀን ካህኑ አኪያ ኤፉድ ለብሶ በእስራኤል ሕዝብ ፊት ነበር፤ ሳኦል ከካህኑ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ፥ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር የተነሣው ሁከትና ሽብር እየባሰበት ሄደ፤ ሳኦልም ካህኑን “እግዚአብሔርን ለመጠየቅ አሁን ጊዜ የለንም” አለው። ከዚህ በኋላ ሳኦልና ወታደሮቹ ካሉበት በመንቀሳቀስ ወደ ውጊያው ሄዱ፦ እዚያም ፍልስጥኤማውያን ግራ በመጋባት እርስ በርሳቸው በሰይፍ ይጋደሉ ነበር። ከፍልስጥኤማውያን ጋር በመተባበር ወደ ጦሩ ሰፈር ሄደው የነበሩ አንዳንድ ዕብራውያንም ፍልስጥኤማውያንን ከድተው ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ተባበሩ። በኤፍሬም ኮረብታዎች ተደብቀው የነበሩ ሌሎች እስራኤላውያንም ፍልስጥኤማውያን በሽሽት ላይ መሆናቸውን ሰሙ፤ ስለዚህም ከወገን ጦር ጋር ተባብረው ፍልስጥኤማውያንን ማሳደድ ጀመሩ፤ እስከ ቤትአዌን ከተማ ማዶ ባለው መንገድ ሁሉ ተከታትለው ወጉአቸው፤ እግዚአብሔርም በዚያን ቀን እስራኤልን በመታደግ አዳነ።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች