የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ከዳዊት ጋር ወዳጅነቱን አጽንቶ ቈይቶ ነበር፤ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት እግር መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ መልእክተኞቹን ላከ፤ ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፤ “አባቴ ዳዊት በዙሪያው ከነበሩት የጠላት አገሮች ሠራዊት ጋር ሲዋጋ መኖሩን አንተ ራስህ ታውቀዋለህ፤ በጠላቶቹ ላይ ድልን እስኪያጐናጽፈው ድረስ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት አለመቻሉንም ታስታውሳለህ፤ አሁን ግን አምላኬ እግዚአብሔር በሀገሬ ድንበር ዙሪያ ሁሉ ሰላም ሰጥቶኛል፤ ምንም ዐይነት አደጋ የሚጥል ጠላት የለብኝም፤ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት ‘ከአንተ በኋላ የማነግሠው ልጅህ ለእኔ ቤተ መቅደስ ይሠራልኛል’ ሲል ተስፋ ሰጥቶት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት እነሆ፥ አሁን ወስኛለሁ፤ ስለዚህ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት የሚቈርጡ ሰዎችን ወደ ሊባኖስ ላክልኝ፤ የእኔም ሰዎች ከእነርሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ አደርጋለሁ፤ ለሰዎችህም አንተ የምትወስነውን ደመወዝ እከፍላለሁ፤ አንተ እንደምታውቀው የእኔ ሰዎች ስለ ዛፍ አቈራረጥ የአንተን ሰዎች ያኽል ዕውቀት የላቸውም።” ኪራም የሰሎሞን መልእክት ሲደርሰው እጅግ ስለ ተደሰተ፥ “በእርሱ እግር ተተክቶ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ እንዲነግሥ ይህን የመሰለ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን!” አለ፤ ከዚህ በኋላ ኪራም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለሰሎሞን ላከ “ያስተላለፍከው መልእክት ደርሶኛል፤ አንተ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤ የሊባኖሱን ዛፍና የዝግባውን ግንድ አዘጋጅቼ አቀርብልሃለሁ፤ የእኔ ሰዎችም ግንዶቹን ከሊባኖስ ወደ ባሕር ያወርዳሉ፤ አንድነት ጠፍረው አስረውም አንተ ወደምትመርጠው ጠረፍ ተንሳፍፈው እንዲደርሱ ያደርጋሉ፤ በዚያም የእኔ ሰዎች ማሰሪያውን ፈተው ለአንተ ሰዎች ያስረክቡአቸዋል፤ አንተም በበኩልህ በቤተ መንግሥቴ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ምግብ በመላክ ፍላጎቴን ታረካለህ።” በዚህ ዐይነት ኪራም ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የሊባኖሱን ዛፍና የዝግባ ግንድ ሁሉ አቀረበለት፤ ሰሎሞንም በበኩሉ በኪራም ቤተ መንግሥት ውስጥ ላሉት ሰዎች ቀለብ የሚሆን ሁለት ሺህ ቶን ስንዴና አራት መቶ ሺህ ሊትር ንጹሕ የወይራ ዘይት በየዓመቱ ይሰጥ ነበር። እግዚአብሔር አስቀድሞ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞን መካከል ሰላም ስለ ነበረ ሁለቱም የጋራ ስምምነት ውል አደረጉ።
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 5:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች