ወዳጆች ሆይ! በዓለም ላይ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ስለ ተነሡ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ይልቅስ መንፈሶች የእግዚአብሔር መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መርምሩ። የእግዚአብሔርን መንፈስ ለይታችሁ የምታውቁት በዚህ ነው፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡን የሚያምን መንፈስ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡን የማያምን መንፈስ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ አይደለም፤ ይህም መንፈስ ይመጣል ሲባል የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው፤ እርሱ አሁን እንኳ በዓለም ላይ አለ። ልጆች ሆይ! እናንተ የእግዚአብሔር ናችሁ፤ በእናንተ ያለው መንፈስ በዓለም ካለው መንፈስ ይበልጣል። ስለዚህ ሐሰተኞች ነቢያትን አሸንፋችኋል። ሐሰተኞች ነቢያት የዓለም ናቸው፤ የሚናገሩትም የዓለምን ነገር ነው። ዓለምም እነርሱን ይሰማቸዋል። እኛ የእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ሁሉ ይሰማናል፤ የእግዚአብሔር ያልሆነ ግን አይሰማንም። እውነተኛን መንፈስና ሐሰተኛን መንፈስ ለይተን የምናውቀው በዚህ ነው። ወዳጆች ሆይ! ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንፋቀር፤ የሚያፈቅር ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። እግዚአብሔር ፍቅር ስለ ሆነ ሰውን የማያፈቅር ሁሉ እግዚአብሔርን አያውቅም። በልጁ አማካይነት ሕይወት እንድናገኝ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል፤ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ መካከል ተገልጦአል። ፍቅር ማለት እንዲህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን ስለ ወደድነው ሳይሆን እርሱ ስለ ወደደንና ኃጢአታችንን እንዲደመስስ ልጁን ስለ ላከልን ነው። ወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔር ይህን ያኽል ካፈቀረን እኛም እርስ በርሳችን መፋቀር ይገባናል። እግዚአብሔርን ያየው ማንም ሰው የለም። እኛ እርስ በርሳችን ብንፋቀር እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል። እግዚአብሔር መንፈሱን ስለ ሰጠን በእርሱ እንደምንኖርና እርሱም በእኛ እንደሚኖር እናውቃለን። አብ የዓለም አዳኝ አድርጎ ወልድን እንደ ላከው አይተናል፤ እንመሰክራለንም። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚያምን ሰው ውስጥ እግዚአብሔር ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ እናምናለንም። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። በዚህ ዓለም እኛ የምንኖረው ልክ ክርስቶስ እንደሚኖረው እንደ መሆኑ ፍቅራችን ፍጹም ቢሆን በፍርድ ቀን ያለ ፍርሀት በፊቱ ለመቅረብ ሙሉ መተማመን ይኖረናል።
1 የዮሐንስ መልእክት 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 የዮሐንስ መልእክት 4:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች